Labels

Showing posts with label ስብከት. Show all posts
Showing posts with label ስብከት. Show all posts

Wednesday, May 29, 2013

እግዚአብሔር አይችልም

እግዚአብሔር አይችልም
በታላቅ ግርማ በማይመረመር እውቀትና በማይቆጠር ጥበብ ለአኗኗሩ መነሻ ለዘመኑ ፍጻሜ የሌለው ብቸኛው አምላክ እግዚአብሔር ነው:: ምንም እንኳ ምድራችን ራሳቸውን በሠራዊት ብዛት፣ በዘመነኛ የጦር መሣሪያና ስልት ያስታተቁ ታላላቅ ተብዬዎች የበዙባት ብትሆንም ትልቅነታቸው ከጌታችን ጋር አይነጻጸርም:: “ጌታችን ታላቅ ነው ኃይሉም ታላቅ ነውና”  እንዲሁም ዓለም የሠለጠነ የሰው ኃይል ቢያከማች የረቀቀ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ቢጠቀም ኃይሉ ግን የሚመጠን፣ የሚለካና የሚገደብ እንዳይቋረጥም ከፍተኛ ጥንቃቄ በተመላበት ቁጥጥር የሚጠበቅ ነው፡፡ የጌታችን ኃይል ግን ከዚህ ይለያል:: ታላቅ ነውና፡፡”እግዚአብሔር ታላቅ ነው” አምላካችን ታላቅ  የተባለው እንደ ፍጥረት ሥርዓት  የሚለካበት መለኪያ ኖሮት አይደለም፡፡በጠንከራ ክንዱ ጊዜና ሥልጣን፣ሐብት፣ትዕቢትና ዕውቀት ያተለቃቸውን ሁሉ በረቂቅ ጥበቡ የሚያሳንስ  እርሱ ስለሆነ ነው፡፡  የቋንቋችንም አድማስ ከዚህ ቃል ማለፍ አይችልም፡፡ ደግሞስ “አቤቱ አንተ ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህ” አይደል የተባለው፡፡መዝ 95፥4፣85፥10
አዎ የእኛ ጌታ እጁን ዘርግቶ ይቅርና ከአንደበቱ ቃል ሳይወጣ በልቡ ፈቃድ ብቻ የገዘፈውን ሰማይና ምድር የሠራ ነው:: በየትኛውም ዘመን ትውልድ የአስተሳሰብ እድገት ሊደርስበት የማይችል ብርሃንን በይሁንታ የፈጠረ ነው፡፡ ለምድር ኪስ አበጅቶ ሰፊ ባደረገው ኪሷ ያስቀመጠውን ውሃ ውቅያኖስ ያለው በጠባቦቹ ኪሶቿ ያስቀመጠውን ውሃ ደግሞ ባሕር  እያለ የጠራው  እርሱ ነው :: ዘርዝረን የማንፈጽመውን ሥራዎቹን ያከናወነበትን ኃይል ደግሞ ከነቢዩ ጋር “ኃይልህ ታላቅ ነው አንተ ባሕርን በኃይልህ አጸናሃት” እንዲሁም “ኃይልህ ብዙ ነው” እንለዋለን፡፡ መዝ 65፥3 ፣73፥13
እግዚአብሔር እርሱ ሠርቶ ይቅርና ሲያሠራም ኃይሉ ታላቅ ነው:: በሙሴ በትር ላይ የተገለጠው ኃይሉ ባሕር ሲከፍል ከዓለት ላይ ውሃ ሲያፈልቅ በእምነት አይተናል:: በእስራኤል ጩኸት ውስጥ የኢያሪኮን ቅጥር /ግንብ/ ሲያፈርስ አስተውለናል:: “ለእግዚአብሔር ዘምሩ የኃይል ቃል የሆነ ቃሉን እነኾ ይሰጣል” ተብሏል  መዝ 67፥33:: ደግሞስ “እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም” የተባለው በእውነት እንደርሱ ያለ ማንም ስለሌለ ነው :: የባሕሩን ኃይል ሲገዛ ሞገዱንም ጸጥ ሲያደርገው ነፋሱንም ሲገስጽ በፈጠረው ፍጥረት ላይ ከፍተኛው ባለሥልጣን እርሱ ብቻ መሆኑን አስታውቋል:: ፍጥረት ሁሉ የኃይሉ መገለጫ የጥበቡ ማስታወቂያ ነው:: መዝ 88፥9፣ ማቴ 8፥23፤ 27::
እግዚአብሔር ለሚያምኑትና ለሚታመኑበት  ሁሉ ነገሮችን የሚያከናውንበት ኃይል ከጠላት የሚከለሉበት ጋሻ መሆኑን “እግዚአብሐር ኃይሌና ጋሻዬ ነው ልቤ በእርሱ ታመነ እኔም ተረዳሁ” በሚለው ዝማሬ መገንዘብ ጠቃሚ ነው መዝ 27፥7:: የሰው ልጅ በራሱ አንዳች ኃይል ስለሌለው ከአምላኩ የተሰጠውን ተፈጥሮአዊ ኃይል ጠቃሚ በሆነ መንገድ ለማዋል በሕይወቱ ውስጥ እግዚአብሔርን ማኖር አለበት:: “ኃይሌን ወደ አንተ አስጠጋለሁ” በእኔ ውስጥ አንተ እንድትሠራ እፈቅዳለሁ ተብሏል:: እንግዲህ እግዚአብሔር በሕይወታችን የሚኖር ከሆነ ሁለንተናችን በኃይል የተመላ ማስተዋላችንም ጥበብ የበዛበት ይሆናል::