ጸሎት
ሕያው ስም ያለህ፣ሕልውናህን ጊዜ የማይወስነው አንተ እግዚአብሔር ነህና ተመስገን፡፡ ፍጹምነትህ አርዓያችን ነው፡፡ርኅራኄኅ መጽናኛችን ነው፡፡ ምሕረትህ መኖሪያችን ነውና ተመስገን፡፡ በልባችን ውስጥ የሚመላለስው የሰውነት ድካማችን ወደ ክፉው እንዳይወስደን ራሳችንን መግዛት የምንችልበትን ጸጋ አብዛልን፡፡ በሥላሴነትህ ውስጥ ያለውን አንድነትህን እንድንረዳ፣አንድነትህ ውስጥ ያለውን ሦስትነትህን እንድንገነዘብ ዓይነ ልቡናችንን አብራ፡፡በቃልህ ራሳችንን ከማየትና ከመመርመር ይልቅ ሌሎችን እንዳንከስበት ማስተዋልን አብዛልን፡፡ መጻሕፍትን የመመርመርን ጥበብና ያገኘነውን እውነት እንድንጠቀምበት አትጋን፡፡ አሜን
ክፍል ፪
ከሙታን ባስነሣው
ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያን በጻፈው መልዕክቱ “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም” በማለት አብና መንፈስ ቅዱስ ያልሆኑትን እርሱ በተለየአካሉ ሰው ሲሆን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለውን አንዲት ሥልጣን የሚወስድበት ማንም እንደ ሌለና እንደማይኖር አስገንዝቧል፡፡ፊል 2፥6፡፡ እውነት ነው እርሱ ራሱን ባዶ ቢያደርግም ፣የባሪያውን መልክ ቢይዝም፣ራሱን ቢያዋርድና ለመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡
ነገር ግን ጳውሎስ አንዱን አንሺ ሌላውን ተነሺ አንዱን ከሙታን መካከል ቀስቃሽ ሌላውን ተቃስቃሽ እያደረገ የጻፈው ለምንድነው ?::የተፈለገው ቁም ነገር ክርስቶስ ሞቶ ከተቀበረ በኋላ ከሙታን መካከል ተለይቶ መነሣቱን ማወጅ ብቻ አይደለም፡፡የክርስቶስ ትንሣኤ ቀድሞ በተዓምራት ይነሱ እንደነበሩት ሰዎች ተመልሶ ለመሞት አይደለምና፡፡ ነገር ግን የኃጢአትን ኃይል ለመግደልና የሞትን ስልጣን ለመሻር ነው፡፡በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ውስጥ ያለውን ይህንን ታላቅ ኃይል በአይሁድ ዕምነት ልባቸው ለታወረ ሰዎች ለማስገንዘብና በክርስቶስ እንዲያምኑ ለማድረግ ነበር፡፡
“እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ . . .” እያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም ልጅ ቢሆን ከአባቱ ጋር የባሕርይ አንድነት እንዳለው ያስረዳል:: ዕብ 1፥3:: ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌሉ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ብሏል:: ዮሐ 1፥1:: ኢየሱስ ክርስቶስም ራሱ “እኔና አብ አንድ ነን” በማለት በእርሱና በባሕርይ አባቱ በአብ መካከል ያለውን አንድነት ገልጿል:: ዮሐ 10፥30:: ሐዋርያው ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው እግዚአብሔር አብ እንደሆነ መግለጹ ታዲያ በአብና በወልድ መካከል ያለውን መለኮታዊ አንድነት ለመጣስ አይደለም፡፡መልዕክቱ የተጻፈው ስለክርስቶስ የማይገባ ግንዛቤ ለነበራቸው ቢሆን ኖሮ ከላይ የዘረዘርኳቸው ሥነመለኮታዊ እሳቤዎች ሁሉ በተጻፉ ነበር:: የስህተቱን ትምህርት ያመጡት ሕገ ኦሪትን ብንተው ቅጣት ይመጣብናል ብለው የሚፈሩ ሰዎች እንጂ ስለ ክርስቶስ ምንም ግንዛቤ ያልነበራቸው አይደሉም:: ስለዚህም ሐዋርያው የሕግ አስፈላጊነት ሙሉ ለሙሉ መቅረቱን ግልጽ አድርጎ ለማስገንዘብና በዚህ ፈንታ በክርስቶስ መስቀልና ትንሣኤ ሁሉም ነገር ተሟልቶ መስጠቱን አጥርቶ ለማስረዳት ነው ::
ዓላማው የክርስቶስን መለኮትነት ማስረዳት ቢሆን ኖሮ እርሱም እንደ ወንገሌላዊው ዮሐንስ በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ እያለ የቃልን /የክርስቶስን/ እግዚአብሔርነት ብቻ አጉልቶና በሦስቱ አካላት መካከል ምንም ልዩነት እንደሌለ አሳይቶ ሐሳቡን መጠቅለል ይችል ነበር:: የክርስቶስን መለኮታዊነት ብቻ አጉልቶ መናገር በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የሚጨምረው ነገር የለም:: ስለእግዚአብሔር እግዚአብሔርነት ጥንትም ሲነገር ነበርና:: ነገር ግን “ከሙታን ባስነሣው” የሚለው ሐረግ የሰው ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘውን ትልቅ ጥቅም የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ለመነሣት ኃይል የሌለው መሆኑን አይደለም የሚናገረው፡፡ መቼም በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ምድራዊና ሟች የሆነ ሰውነት የተሸከሙ ሰዎች በጥላቸው ሙታን እያስነሱ፤ በጨርቃቸው ድውይ እየፈወሱ ኢየሱስ ሞትን ድል ማድረግ አቃተው ብሎ ማሰብ እብደት ወይም ጅልነት ነው:: ሐዋ 5፥15፣ 19፥11-14:: ኢየሱስም ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀን አስነሣዋለሁ” እያለ ስለ ሞቱና ትንሣኤው ይናገር ነበር:: ዮሐ 2፥19:: እንዲሁም “ነፍሴን ደግሞ አነሳት ዘንድ አኖራለሁና . እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወሰዳትም” ብሏል:: ዮሐ 10፥18:: ስለዚህም ከሙታን ባስነሳው በእግዚአብሔር አብ በማለት እግዚአብሔር አብ ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን እንዳስነሳው ሲገልጽ፤ ወልድ /ኢየሱስ ክርስቶስ/ ደግሞ መስራት የነበረበትም ነገር አብን ማክበር መሆኑን ማስረዳት ነው:: ኢየሱስ “እኔ ላደረገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ” ብሏል ዮሐ 17፥4::
እንግዲህ ትውልድን በፍርሃት እያስጨነቀ በኃጢአት ምክንያት ሰልጥኖ የነበረው ሞት በክርስቶስ ላይ ለምን ኃይል አጣ? ክርስቶስ በሞት ሥልጣን ቁጥጥር ሥር ውሎ ወደ መቃብር ሲወርድ በአምላክነት ሥልጣኑ ከሞት ባለሥልጣን ጋር በመቃብር ውስጥ ለመታገል ቀጠሮ ይዞ ነበርን? አይደለም:: የክርስቶስ መሞት ዓላማው በአምላክነት ሥልጣኑ ታግሎ ማሸነፍ ቢሆን ኖሮ ቀድሞውኑ መሞት አያስፈልገውም ነበር:: አምላክ ነውና:: ያም ብቻ አይደለም ሥጋን መዋሃድና ሰው መሆን አያስፈልገውም ነበር:: በእግዚአብሔርነቱ ሥልጣን ሥጋን ሳይዋሃድ ሞትን መቅጣት ይችል ነበርና:: ግን አላደረገውም:: በሥልጣኑ ቀላያትን ነድሎ ምድርን በንፍር ውሃ ያጠፋ፣ ሕዝቡን ባሕር ከፍሎ ያሻገረ፣ ጠላትን በባሕር ውስጥ ያሰጠመ፣ በበረሃ መና የሰጠ ሌሊቱን በብርሃን ቀኑን በደመና ሕዝቡን ይመራ የነበረ ከዓለት ላይ ውሃ ያፈልቅ የነበረና ሌሎችንም ዘርዝረን የማንፈጽማቸውን ሥራዎች በመለኮታዊ ሥልጣኑ የሠራ ሞትንም መቅጣት ይችል ነበር::