ጸሎት
ሕያው ስም ያለህ፣ሕልውናህን ጊዜ የማይወስነው አንተ እግዚአብሔር ነህና ተመስገን፡፡ ፍጹምነትህ አርዓያችን ነው፡፡ርኅራኄኅ መጽናኛችን ነው፡፡ ምሕረትህ መኖሪያችን ነውና ተመስገን፡፡ በልባችን ውስጥ የሚመላለስው የሰውነት ድካማችን ወደ ክፉው እንዳይወስደን ራሳችንን መግዛት የምንችልበትን ጸጋ አብዛልን፡፡ በሥላሴነትህ ውስጥ ያለውን አንድነትህን እንድንረዳ፣አንድነትህ ውስጥ ያለውን ሦስትነትህን እንድንገነዘብ ዓይነ ልቡናችንን አብራ፡፡በቃልህ ራሳችንን ከማየትና ከመመርመር ይልቅ ሌሎችን እንዳንከስበት ማስተዋልን አብዛልን፡፡ መጻሕፍትን የመመርመርን ጥበብና ያገኘነውን እውነት እንድንጠቀምበት አትጋን፡፡ አሜን
ክፍል ፪
ከሙታን ባስነሣው
ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ቤተክርስቲያን በጻፈው መልዕክቱ “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም” በማለት አብና መንፈስ ቅዱስ ያልሆኑትን እርሱ በተለየአካሉ ሰው ሲሆን ከአብና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ያለውን አንዲት ሥልጣን የሚወስድበት ማንም እንደ ሌለና እንደማይኖር አስገንዝቧል፡፡ፊል 2፥6፡፡ እውነት ነው እርሱ ራሱን ባዶ ቢያደርግም ፣የባሪያውን መልክ ቢይዝም፣ራሱን ቢያዋርድና ለመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ እግዚአብሔር ነው፡፡
ነገር ግን ጳውሎስ አንዱን አንሺ ሌላውን ተነሺ አንዱን ከሙታን መካከል ቀስቃሽ ሌላውን ተቃስቃሽ እያደረገ የጻፈው ለምንድነው ?::የተፈለገው ቁም ነገር ክርስቶስ ሞቶ ከተቀበረ በኋላ ከሙታን መካከል ተለይቶ መነሣቱን ማወጅ ብቻ አይደለም፡፡የክርስቶስ ትንሣኤ ቀድሞ በተዓምራት ይነሱ እንደነበሩት ሰዎች ተመልሶ ለመሞት አይደለምና፡፡ ነገር ግን የኃጢአትን ኃይል ለመግደልና የሞትን ስልጣን ለመሻር ነው፡፡በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ውስጥ ያለውን ይህንን ታላቅ ኃይል በአይሁድ ዕምነት ልባቸው ለታወረ ሰዎች ለማስገንዘብና በክርስቶስ እንዲያምኑ ለማድረግ ነበር፡፡
“እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ . . .” እያለ ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም ልጅ ቢሆን ከአባቱ ጋር የባሕርይ አንድነት እንዳለው ያስረዳል:: ዕብ 1፥3:: ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌሉ “በመጀመሪያው ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ፤ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ” ብሏል:: ዮሐ 1፥1:: ኢየሱስ ክርስቶስም ራሱ “እኔና አብ አንድ ነን” በማለት በእርሱና በባሕርይ አባቱ በአብ መካከል ያለውን አንድነት ገልጿል:: ዮሐ 10፥30:: ሐዋርያው ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን ያስነሣው እግዚአብሔር አብ እንደሆነ መግለጹ ታዲያ በአብና በወልድ መካከል ያለውን መለኮታዊ አንድነት ለመጣስ አይደለም፡፡መልዕክቱ የተጻፈው ስለክርስቶስ የማይገባ ግንዛቤ ለነበራቸው ቢሆን ኖሮ ከላይ የዘረዘርኳቸው ሥነመለኮታዊ እሳቤዎች ሁሉ በተጻፉ ነበር:: የስህተቱን ትምህርት ያመጡት ሕገ ኦሪትን ብንተው ቅጣት ይመጣብናል ብለው የሚፈሩ ሰዎች እንጂ ስለ ክርስቶስ ምንም ግንዛቤ ያልነበራቸው አይደሉም:: ስለዚህም ሐዋርያው የሕግ አስፈላጊነት ሙሉ ለሙሉ መቅረቱን ግልጽ አድርጎ ለማስገንዘብና በዚህ ፈንታ በክርስቶስ መስቀልና ትንሣኤ ሁሉም ነገር ተሟልቶ መስጠቱን አጥርቶ ለማስረዳት ነው ::
ዓላማው የክርስቶስን መለኮትነት ማስረዳት ቢሆን ኖሮ እርሱም እንደ ወንገሌላዊው ዮሐንስ በመጀመሪያ ቃል ነበረ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ እያለ የቃልን /የክርስቶስን/ እግዚአብሔርነት ብቻ አጉልቶና በሦስቱ አካላት መካከል ምንም ልዩነት እንደሌለ አሳይቶ ሐሳቡን መጠቅለል ይችል ነበር:: የክርስቶስን መለኮታዊነት ብቻ አጉልቶ መናገር በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የሚጨምረው ነገር የለም:: ስለእግዚአብሔር እግዚአብሔርነት ጥንትም ሲነገር ነበርና:: ነገር ግን “ከሙታን ባስነሣው” የሚለው ሐረግ የሰው ልጅ በኢየሱስ ክርስቶስ ያገኘውን ትልቅ ጥቅም የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ሆኖም ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ለመነሣት ኃይል የሌለው መሆኑን አይደለም የሚናገረው፡፡ መቼም በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ምድራዊና ሟች የሆነ ሰውነት የተሸከሙ ሰዎች በጥላቸው ሙታን እያስነሱ፤ በጨርቃቸው ድውይ እየፈወሱ ኢየሱስ ሞትን ድል ማድረግ አቃተው ብሎ ማሰብ እብደት ወይም ጅልነት ነው:: ሐዋ 5፥15፣ 19፥11-14:: ኢየሱስም ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት በሦስት ቀን አስነሣዋለሁ” እያለ ስለ ሞቱና ትንሣኤው ይናገር ነበር:: ዮሐ 2፥19:: እንዲሁም “ነፍሴን ደግሞ አነሳት ዘንድ አኖራለሁና . እኔ በፈቃዴ አኖራታለሁ እንጂ ከእኔ ማንም አይወሰዳትም” ብሏል:: ዮሐ 10፥18:: ስለዚህም ከሙታን ባስነሳው በእግዚአብሔር አብ በማለት እግዚአብሔር አብ ኢየሱስ ክርስቶስን ከሙታን እንዳስነሳው ሲገልጽ፤ ወልድ /ኢየሱስ ክርስቶስ/ ደግሞ መስራት የነበረበትም ነገር አብን ማክበር መሆኑን ማስረዳት ነው:: ኢየሱስ “እኔ ላደረገው የሰጠኸኝን ሥራ ፈጽሜ በምድር አከበርሁህ” ብሏል ዮሐ 17፥4::
እንግዲህ ትውልድን በፍርሃት እያስጨነቀ በኃጢአት ምክንያት ሰልጥኖ የነበረው ሞት በክርስቶስ ላይ ለምን ኃይል አጣ? ክርስቶስ በሞት ሥልጣን ቁጥጥር ሥር ውሎ ወደ መቃብር ሲወርድ በአምላክነት ሥልጣኑ ከሞት ባለሥልጣን ጋር በመቃብር ውስጥ ለመታገል ቀጠሮ ይዞ ነበርን? አይደለም:: የክርስቶስ መሞት ዓላማው በአምላክነት ሥልጣኑ ታግሎ ማሸነፍ ቢሆን ኖሮ ቀድሞውኑ መሞት አያስፈልገውም ነበር:: አምላክ ነውና:: ያም ብቻ አይደለም ሥጋን መዋሃድና ሰው መሆን አያስፈልገውም ነበር:: በእግዚአብሔርነቱ ሥልጣን ሥጋን ሳይዋሃድ ሞትን መቅጣት ይችል ነበርና:: ግን አላደረገውም:: በሥልጣኑ ቀላያትን ነድሎ ምድርን በንፍር ውሃ ያጠፋ፣ ሕዝቡን ባሕር ከፍሎ ያሻገረ፣ ጠላትን በባሕር ውስጥ ያሰጠመ፣ በበረሃ መና የሰጠ ሌሊቱን በብርሃን ቀኑን በደመና ሕዝቡን ይመራ የነበረ ከዓለት ላይ ውሃ ያፈልቅ የነበረና ሌሎችንም ዘርዝረን የማንፈጽማቸውን ሥራዎች በመለኮታዊ ሥልጣኑ የሠራ ሞትንም መቅጣት ይችል ነበር::
እንግዲህ ሐዋርያው ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አብ ሲል ቅዱስ ሉቃስም “እግዚአብሔር ግን የሞትን ጣር አጥፍቶ አስነሣው ሞት ይይዘው ዘንድ አልቻለምና” እያሉ ክርስቶስን ከሞት ያስነሣው እግዚአብሔር አብ እንደሆነ ይገልጻሉ:: ሐዋ 2፥24:: ይህ ማለት የአብ የወልድ የመንፈስ ቅዱስን ሥልጣን መለያየት አይደለም:: ኢየሱስ ክርስቶስ ከእግዚአብሔር ዘንድ እግዚአብሔርነትን መቀማት እንደሚገባ ሳይቆጥር የተገለጠ ሰው ነው:: የእግዚአብሔርነቱን ኃይል ሙት በማንሣት፣ ዕውር በማብራት፣ ነፋሳትን በመገሰጽና ማዕበሉን ጸጥ በማድረግ ፣ አጋንንትን በማውጣት አሳይቷል:: ሰውነቱንም በሚታይ በሚዳሰስ ማንነት በሰው መካከል ተወልዶ፣ አድጎ እየተመላለሰ ፣እያንቀላፋ፣ እየበላ፣ እየጠጣ፣ እያዘነ ፣እያለቀሰ አሳይቷል፡ ፡
ለመሆኑ ሞት ኢያሱስ ክርስቶስን በመቃብር ውስጥ ይዞ ማስቀረት ለምን አልቻለም ? ምክንያቱም ሞት ትውልድን የሚይዝበት እጁ ኃጢአት ነበር፡፡ ሐዋርያው “የሞት መውጊያ ኃጢአት ነው፡ የኃጢአትም ኃይል ሕግ ነው”ይላል፡፡ ኃጢአት ኃይልን ከሕግ የሚያገኘው እንዴት ነው ? ሕግ ዋናው ሥራው ኃጢአት መግለጥ ስለሆነ ነው፡፡1ቆሮ 15፥56 ጌታ ኢየሱስም የሚከሰስበት አንዳች ኃጢአት ስለሌለው ሞት በኢየሱስ ላይ አቅም አጣ፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ስለ ወንጌል ማብራሪያ ሲሰጥ “ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለተገለጠ ስለ ልጁ ነው:: እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ይላል፡፡ ሮሜ 1፥4:: ሐዋርያው ክርስቶስ ኢየሱስ በሥጋና በደም ማንነታችንን የተካፈለ/ሰው የሆነ/መሆኑንና ከዳዊት ዘር መምጣቱን በተፈጥሮ ላይ ሥልጣኑን /ኃይሉን/ ያሳይ ሥለነበር የእግዚአብሔር ልጅነቱን አስረድቷል፡፡ ስለትንሣኤው ሲገልጽ ግን “እንደ ቅድስና መንፈስ ከሙታን መነሣት የተነሣ” ይለዋል፡፡
ጻድቅ የለም አንድስ እንኳ ተብሎ በተነገረበት በሰው ዘር ውስጥ የተገኘ ብቸኛው ንጹሕ ሰው ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ይህንንም ጌታን የሸጠው የአስቆሮቱ ይሁዳ “ንጹህ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ” እያለ ገልጾታል፡፡ የመስፍኑ ጲላጦስ ሚስት ደግሞ “ጻድቅ ሰው” መሆኑን በሕልሟ ስላየች ለማለቤቷ መልዕክት ልካለታለች፡፡ ራሱ ጲላጦስም ምንም እንኳ ኢየሱስን ገርፎ ይሰቅሉት ዘንድ አሳልፎ የሰጠ ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ “ጻድቅ ሰው” መሆኑን መስክሯል፡፡ ማቴ 27፥4፣ 19_25 ፡፡ቅዱስ ጴጥሮስ በመልዕክቱ “እርሱም ኃጢአት አላደረገም ተንኮልም በአፉ አልተገኘበትም ሲሰድቡትም መልሶ አልተሳደበም መከራም ሲቀበል አልዛተም” እያለ በሐሳቡ፣በአንደበቱና በተግባሩ ንጹሕና ቅዱስ ሰው መሆኑን አስረድቷል፡፡ 1ጴጥ 2፥22_2፡፡እንደ ሰውነቱ የሞትን ጽዋ ቢቀምስና ወደ መቃብር ቢወርድም ቅድስናው እና ንጽሕናው ከሞት ኃይልና ሥልጣን በላይ እንዲሆን ስላደረገው ከሙታን መካከል ተነስቷል፡፡ መላእክቱም በበደልና በኃጢአት ሙት በነበረው ትውልድ መካከል የተገኘ ብቸኛው ጻድቅ እርሱ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ሲገልጹ “ ሕያውን ከሙታን መካከል ስለምን ትፈልጉታላችሁ ? ተነስቷል እንጂ በዚህ የለም ብለዋል፡፡ ሉቃ 24፥5 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ንጹሕና ቅዱስ ሰው ስለሆነ ከሙታን መካከል ተነስቷል፡፡ መዝሙረኛው ዳዊትም “ቅዱስህንም መበስበስን ያይ ዘንድ አትተወውም” በማለት ትንቢት የተናገረው ለጌታ ኢየሱስ ነበር፡፡ መዝ 15 ፥8_11
ገላ 1፥2 : ከእኔም ጋር ያሉ ወንድሞች ሁሉ ወደ ገላትያ አብያተ ክስቲያናት
ሐዋርያው ጳውሎስ ሌሎች መልዕክታትን ሲጽፍ በመግቢያው ላይ የሚጠቀምባቸው ሐረጎች የተለመዱ ነበሩ:: አብረውት ያሉትንና በአገልግሎቱ የሚራዱት ካሉ በግልጽ ስማቸውን ይጠቅሳል:: በዛውም ስንት ሰው ከእርሱ ጋር እንዳለ ይታወቅ ነበር:: በዚህ መልክዕክቱ ግን የማንንም ስም ሳይጠቅስ ወንጌልን አስተምሯቸው በክርስቶስ ያመኑትን ከእኔም ጋር ያሉ ወንድሞች ሁሉ እያለ ይገልጻል:: በአካል አብረውት ባይሆኑ በመንፈስ ኅብረት አላቸውና:: እንዲሁም በገላትያ ቤተክርስቲያን ውስጥ የተነዛውን ኑፋቄ ወንጌልን በእውነት የተረዱ ሁሉ እንደሚቃወሙት በማመን ወንድሞች ብሎ ጠቅሷል:: ይህንንም ያደረገበት ምክንያት ሐሰተኛ ወንድሞች እርሱ ብቻውን ነው፣ በእርሱ ትምህርት ከእርሱ ጋር የሚስማሙ ሌሎች ወንድሞች /ሐዋርያት/ የሉም፣ ደግሞ የእርሱ ትምህርት ልብ ወለድ /አዲስ ትምህርት/ ነው እያሉ ስሙን ማጥፋት ጀምረው ነበረ:: ስለዚህ እርሱ ብቻውን አለመሆኑንና በትምህርቱም የሚስማሙ ብዙ ወንድሞች አብረውት መኖራቸውን አስረድቶ በእርሱ ላይ ያላቸውን ጥርጣሬ ለማስወገድ ነው::
ወደ ገላትያ ቤተክርስቲያን
ወንጌል ያለ ኦሪት ፤ ግዝረት ያለ ጥምቀት አያድንም የሚለው የአንዳንድ አይሁድ ክርስቲያኖች የስህተት አስተምህሮ የገላትያ አብያተክርስቲያናት ውስጥ ተሰራጭቶ ነበር:: “ወደ ገላትያ አብያተክርስቲያናት” የሚለው ንግግር የሐዋርያውን ቁጣ ነው የሚያመለክተው:: ሐዋርያው ጳውሎስ በሌሎች መልዕክቶቹ መግቢያ ላይ የሚታወቀው ፍቅር፣ ክብርና ቅድስናን የሚያመለክቱ ዓረፍተ ነገሮችን በመናገር ነበር:: ለምሳሌ:
v ለቆሮንቶስ ምዕመናን:
“. . . በቆሮንቶስ ላለች ለእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን በክርስቶስ ኢየሱስ ለተቀደሱት . . .”1ቆሮ 1፥2
v ለሮም ቤተክርስቲያን
“. . . የኢየሱስ ክርስቶስ ልትሆኑ የተጠራችሁ . . . በእግዚአብሔር ለተወደዳችሁና ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁ . . .”
ሮሜ 1፥6
v ለኤፌሶን ቤተክርስቲያን
“በኤፌሶን ላሉት ቅዱሳን በክርስቶስ ኢየሱስም ላሉት ምዕመናን” ኤፌ 1፥1
በማለት ለመልዕክታቱ መግቢያ ይጠቀም ነበር ፡፡
ለገላትያ ቤተክርስቲያን ሲጽፍ ግን “ለእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን” “ለተወደዳችሁ ቅዱሳን” የክብርና የፍቅር ንግግር መናገር አልፈለገም:: እነዚህን ቅጽሎች አለመጠቀሙ ለገላትያ ቤተክርስቲያን የነበረው ፍቅርና ክብር ጎድሎበታል ማለት ነው:: አንድ ክርስቲያን (ምዕመን) የዳነ፣ የጸደቀ መሆኑን ካላወቀ /ካላመነ/፤ በሌላ መልኩ ደግሞ ድኅነቱና ጽድቁ በእግዚአብሔር ጸጋ የተከነናወነ መሆኑን ካልተረዳ አለ ለማለት ያስቸግራል::
የገላትያ ምዕመናን ዕምነት በጸጋ እንዳዳናቸው ማመናቸውን ትተው ድኅነትና ጽድቅ የሚገኘው ሕግን በመፈጸም ነው ወደሚለው ትምህርት ልባቸው እያዘነበለ ስለመጣ ለሐዋርያው እንዲሁ ስብስብ ብቻ ሆኑበት:: የቆሮንቶስ ምዕመናን በሥነ ምግባር ጉድለት ቢያሳዝኑት “እንዲሁ ሰው ብቻ መሆናችሁ አይደለምን?” እንዳላቸው የገላትያ ክርስቲያኖችም ስም ያላቸው ነገር ግን በመንፈስ የሞቱ ሆኑበት:: ስለዚህም ቅዱሳን የተወደዱና የእግዚአብሔር የመሆናቸው ጉዳይ ገና መጠናት ነበረበት:: መሸከም ያልቻሉትን ስም ሊሰጣቸው አልወደደምና:: “ወደ ገላትያ ቤተክርስቲያን” ብሎ ጻፈ:: ሰው ከወንጌል ጋር በተለያየ አስተሳሰብና አመለካከት ከተለያየ “የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን”የሚለውን ስያሜ አያሟላም:: የእግዚአብሔር ቤተክርስቲያን በእውነት አምድና መሠረት ላይ የቆመች ከእግዚአብሔር ሐሳብ ጋር የሚስማማ ሀሳብ ያላት ማለት ናትና::
v ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን
ክርስቲያን ያለ እግዚአብሔር ጸጋና ሰላም መኖር አይችልም:: የገላትያ ክርስቲያኖች ደግሞ ለዘለዓለም መዳን ይሆንላቸው ዘንድ እግዚአብሔር በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሰጠውን ጸጋ ቸል ብለዋል:: ይህ ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር ያጣላል:: “የእግዚአብሔርን ልጅ የረገጠ ያንንም የተቀደሰበትን የኪዳኑን ደም እንደ ርኩስ ነገር የቆጠረ የጸጋውንም መንፈስ ያክፋፋ እንዴት ይልቅ የሚብስ ቅጣት የሚገባው ይመስላችኋል” ተብሏልና ዕብ 10፥29:: እነርሱም በጸጋ የተገኘውን ድኅነት በሥራ እንደሚገኝ አድርገው ወደ ማመን ስለመጡ ከጸጋ ተራቁተዋልና ሐዋርያው ጸለየላቸው:: እነርሱ እየተጓዙ ያሉበት መንገድ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያጣላ ስለሆነ የገፉትን ጸጋ ማግኘት እንዲችሉ ልባቸው በዚያው እንዲያርፍ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን ብሏቸዋል::
ጸጋ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን በጎነትና ንጹሕ ፍቅር የተቀበልንበት ነው:: እንዲሁ መወደዳችን ጠላቶች ሳለን በልጁ ሞት መታረቃችን ሊመዘን የማይችል ጸጋ ነው:: ዮሐ 3፥16፣ ሮሜ 5፥10:: ሳይገባችሁ የተሰጣችሁ የእግዚአብሔር ስጦታ ይጽናላችሁ ብሏል::
ሰላም የውስጥ ዕረፍት ነው:: የተረጋጋ አእምሮ የሰከነ ስሜት ለመንፈስ ቅዱስ አሠራር የተመቻቸ ፈቃድ ውስጥ የሚገኝ የውስጥ ጸጥታ ነው:: ክርስቶስ ከእርሱ የሚገኘውን ሰላም ዓለም ከምትሰጠው ሰላም ጋር አነጻጽሮ እርሱ የሚሰጠው ሰላም ከዓለም ሊገኝ እንደማይችል አስረግጦ ተናግሯል:: ዮሐ 14፥27:: “ሰላምን እተውላችኋለሁ፣ ሰላሜን እሰጠችኋለሁ፤ እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጥ አይደለም” ብሏል:: እርሱ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ ያለው ላመኑበት ነው:: በክርስቶስ ኢየሱስ ያመኑ ብቻ የእርሱ ሰላም ይደርሳቸዋል:: ሐዋርያውም “እንግዲህ በእምነት ከጸደቅን በእግዚአብሔር ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ሰላምን እንያዝ” ብሏል:: ሮሜ 5፥1:: በክርስቶስ የተሰጠን ሰላም ከእግዚአብሔር ጋር ተወዳጅተን የምንኖርበት ነው:: “በመስቀሉ ደም ሰላምን አድርጎ በምድር ወይም በሰማያት ያሉትን ለራሱ እንዲያስታርቅ ፈቅዷል”፡፡ ይገርማል! በደም የተገኘ ሰላም!!!:: በክርስቶስ የተገኘው ሰላም ዋጋው ይህን ያህል ለምን ውድ ሆነ? ሊመጠንና ሊመረመረ የማይችል ፍቅርን ለማስረዳት ነው:: ከእርሱ የተገኘው ሰላም አእምሮን ሁሉ የሚያልፍ ነው:: ተመን የለውም:: ቈላ 1፥20:: የደም ዋጋ ስለተከፈለ ነው ከእግዚአብሔር ጋር ሰላምን ያገኘነው:: ዓለም ሰላም የላትም አልተባለም:: በራሷ መስፈርት ለራሷ የሚስማማ ሰላም አላት:: ሆኖም ግን ከክርስቶስ የሚገኘው ሰላም ይበልጣል፤ ሰላምን እሰጣችኋለሁ ካለ በኋላ ይህ የተሰጠን ሰላም ደግሞ የራሱ መሆኑን ለማስገንዘብ “ሰላሜን እሰጣችኋለሁ” ብሏል:: የዓለም ሰላም ከናፍቆትና ከምኞት መግለጫነት የማያልፍ፣ታይቶም የሚጠፋ ነው:: ሐዋርያው በዚህ ሐዋርያዊ ቡራኬው መግቢያውን ይጠቀልላል፡፡
ዓለም ሰላምን ለማግኘት በማኅበራዊ ዘርፍ በከፍተኛ ደረጃ ጥናት ያደረጉ ምሁራንን ከፍተኛ ባለስልጣናትንና ዕድሜና ኑሮ ያስተማራቸውን አዛውንት እንዲሁም በብልጥግና ውስጥ ያሉ ባለጠጎችንና በተለያዩ የስምሪት መስኮች ዝነኛ የሆኑ ባለሙያዎችን ትሰበስባለች:: ባማረ ሕንጻ ውስጥ በተመቻቹ መንበሮችና ጠረጴዛዎች ዙሪያ ውይይቱ ድርድሩ ይካሄዳል:: የአቋም መግለጫም ይረቀቃል:: ይሁን እንጂ ማኅበራዊ ደኅንነትን ሊያስጠብቅ የሚችል ሰላም ሊመጣ አልቻለም:: አይመጣምም:: ስለ ሰላም ውይይት በሚካሄድበት ሰዓት ስብሰባው ውስጥም ሆነ ከዛ ውጭ ሰላም የለም:: በብዙ ንትርክና ድርድር በረቀቁ አስተሳሰቦችና በበሰሉ ንግግሮች ሰላም የሚገኝ ይመስላል:: ግን አይገኝም:: የሰላም አለቃ ከሆነው ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ብቻ በመስማማት ነው የሚገኘው:: ኢሳ 9፥6፣ 26፥3::
ሐዋርያው ለምዕመናን እንዲደርሳቸው የፈለገው ጸጋና ሰላም “ከእግዚአብሔር ከአባታችን ከጌታችንም ከኢየሱስ ክርስቶስ” የሚገኘውን ነው፡፡ሰው እግዚአብሔርን በአምላክነት፣በፈጣሪነት ቢያውቀውም በአባትነትና በልጅነት ፍቅር የተሳሰረበት ጊዜ ግን አልነበረም፡፡ከኢየሱስ ክርስቶስ በሥጋ መገለጥ አስቀድሞ እስራኤል እግዚአብሔርን አባታችን ቢሉትም በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የነበረው ቃል ኪዳን ብቻ ነበር፡፡ ቃል ኪዳን ደግሞ የመንፈስ ትስስርን የሚያጸና ነው፡፡ይሁን እንጂ በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔርን አባታችን ስንለው በብሉይ ከነበረውና በቃል ኪዳን ከጸናው የመንፈስ ትስስር የሚያልፍ እውነት አለ፡፡ ያም እውነት የእግዚአብሔር ቃል ሰው መሆን ነው፡፡ቃል/ ኢየሱስ/ ሰው ከሆነበት ጊዜ ጀምሮ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል የሥጋ ዝምድና ተፈጠረ፡፡”እኛ ደግሞ ዘመዶቹ ነን...... በእርሱ ሕያዋን ነንና እንንቀሳቀሳለን እንኖርማለን፡፡ የእግዚአብሔር ዘመዶች ከሆን........ “ ሐዋ 17፥28 ይላል፡፡ እንዲሁም “የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም.............በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው” ተብሏል፡፡ ዕብ 2፥16–17፡፡ አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ ሰው በመሆኑ ምክንያት እርሱን አዳኝና ቤዛ አድርጎ ያመነ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኗል ፡፡ ይሆናልም፡፡” በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢያሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ” ገላ 3፥26 ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን የሚገኘው ልጅነት ከወንድ ዘር ከእናት እንደሚገኘው ልጅነት በሞት የሚሻር የሚጠፋ አይደለም፤ወይም ሌላ ልጅ ወልደው አባት/ እናት/ የሚኮንበት ሳይሆን እንዲሁ ልጅ በመሆን የሚኖርበት ነው፡፡ ይህ መንፈሳዊ ልጅነት እንዴት እንደሚገኝ ቅዱስ ጴጥሮስ “ ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም በሕያውና ለዘላለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ፡፡” ይላል፡፡ 1ጴጥ 1፥23
ስለዚህ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አባት የሆነው እግዚአብሔር የአንድ ልጁን ጌትነት ላመንን ለእኛ ደግሞ በጸጋ አባት ሆኖናል፡፡ ጌታ ኢየሱም ከትንሳኤው በኋላ “ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ............ ዐርጋለሁ” ብሏል፡፡ ነገር ግን ወደ አባታችን ዐርጋለሁ ለምን አላለም ? ምክንያቱ የእግዚአብሔር አባትነት ለእኛና ለእርሱ ስለሚለያይ ነው፡፡ ለእርሱ የባሕርይ ለእኛ የጸጋ አባት ነውና፡፡
ጸጋ ይብዛላችሁ !!!!
No comments:
Post a Comment