ክፍል ሦስት
“ራሱን ሰጠ”
“ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችንና እንደ አባታችን ፈቃድ
ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ” ገላ 1፥4
አሁን የሚለው የጊዜ ቀመር ስያሜ ቀጣይ የሆነ የሕይወት ዑደት ማኅተም ነው:: እኔ አሁን የሚለውን ቃል ለመጻፍ ስጀምር አሁን ነበር:: ስላለፍኩት ደግሞ ቅድም ሆኗል:: የአሁኑ አሁን ቅድም የሚለውን ቃል ለመጻፍ ነው ያገለገለኝ:: መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ እስትንፋስ እንደመሆኑ አጠቃላይ መልዕክቱ ከጊዜ አንጻር ሲተመን አሁን በተባለው ጊዜ ላይ ልዩ ትኩረት አለው:: ዛሬ ሃያ አራት ሰዓታትን ሲይዝ አሁን ግን ያለንበትን ቅጽበት ብቻ የሚወክል ነው:: ባለፈውና በሚመጣው ቅጽበት መካከል ያለች ሰዓት የማንነታችን ልዩ መገለጫ ናት::
በሕይወት ውጣ ውረድ ውስጥ
የሚፈራረቁ አዎንታዊና አሉታዊ ነገሮች ሁሉ እየተከሰቱ የሚያልፉት ቅድም፣አሁንና ኋላ
በተባሉት የጊዜ ሰንሰለታማ ሂደት ውስጥ ነው ፡፡ሐዋርያው ቅድም የነበርንበት፣ አሁን ያለንበትና ጌታ ቢፈቅድ በኋላ የምንኖርበት
ይህ ዓለም ክፉ እንደሆነ ይገልጻል:: የአሁኑ ዓለም መልካምና ክፉ ነገር ሊከናወንበት ይችላል:: አዲሱ ሰው ክርስቶስን ለብሰው
እርሱ ውበት መልክ የሆናቸው ሁሉ መልካሙን ያደርጋሉ:: አንድ ጊዜ በክርስቶስ ስለጸደቁ ራሳቸውን የክፉ ነገር ባርያ አያደርጉም
የክርስቶ ልብ አላቸውና :: ከክርስቶስ
ውጭ ያሉት ደግሞ ክፉን ያደርጋሉ:: የክፉ ድርጊት መነሻው በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ አለማመን ነው:: የአሁኑ ዓለም ተብሎ የተገለጸው
የዕለትተዕለት የሰው ኑሮ /ሕይወት/ ነው:: የዓለም ክፋ የሚገለጠው በሰው ኑሮ ውስጥ ነውና::አሁን የሚለው የጊዜ ቀመር ስያሜ ቀጣይ የሆነ የሕይወት ዑደት ማኅተም ነው:: እኔ አሁን የሚለውን ቃል ለመጻፍ ስጀምር አሁን ነበር:: ስላለፍኩት ደግሞ ቅድም ሆኗል:: የአሁኑ አሁን ቅድም የሚለውን ቃል ለመጻፍ ነው ያገለገለኝ:: መጽሐፍ ቅዱስ መለኮታዊ እስትንፋስ እንደመሆኑ አጠቃላይ መልዕክቱ ከጊዜ አንጻር ሲተመን አሁን በተባለው ጊዜ ላይ ልዩ ትኩረት አለው:: ዛሬ ሃያ አራት ሰዓታትን ሲይዝ አሁን ግን ያለንበትን ቅጽበት ብቻ የሚወክል ነው:: ባለፈውና በሚመጣው ቅጽበት መካከል ያለች ሰዓት የማንነታችን ልዩ መገለጫ ናት::
ዓለም ክፉ የተባለበት ምክንያት
ገዥውም ክፉ ስለሆነው ነው:: እርሱ ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ በሰው ማንነት ውስጥ የገባውን የክፋት አስተሳሰብና አመለካከት እንዲሁም የክፋት ስሜት እየተጠቀመ
የዓለምን ሥርዓት በነውር ሥራዎች እየመላ ብዙዎችን ለዘላለም ጥፋት ያሚመራ ነው፡፡ “ዓለምም በሞላው በክፉ እንደተያዘ እናውቃለን”
1ዮሐ 5፥19:: እንዲሁም “የዚህዓለም አምላክ የማያምኑትን ሐሳብ አሳወረ” ተብሏል:: 2ቆሮ 4፥4:: የዚህ ዓለም አምላክ የተባለው
ዲያብሎስ ነው:: እርሱ ደግሞ ሰው የልቡናው ዐይን እንዳይበራና የተደረገለትን መዳን እንዳይረዳ ይፈትናል፤ ያደርጋልም:: ከክርስቶስ
መንግሥት ውጭ ያሉ በዲያብሎስ ግዛት ውስጥ የሚኖሩ ብዙዎች በራሳቸው ክበብ ውስጥ የሐሰት ሰላምና ፍቅር አላቸው:: ጌታም ይህን ለማስረዳት እኔ የምሰጣችሁ ሰላም ዓለም እንደሚሰጣችሁ
አይደለም ብሏል:: እንዲሁም “ዓለም የራሱ የሆነውን ይወዳል” ብሏል:: የተረጋጋ የሚመስል ኑሮና መተሳሰብ ያለበት የሚመስል ፍቅር
በብዙ ዓለማውያን ዘንድ ሊታይ ይችላል:: ግን ሁሉም ሐሰት ነው::
እንግዲህ ሐዋርያው ይህን
እውነት ለማስረዳት የአሁኑን ዓለም ኑሮ/ ሕይወት/ ክፉ መሆኑን አስገንዝቧል:: ደግሞም የአሁኑ ዓለም አለ እንጂ ዓለም አላለም::
ምክንያቱም ክርስቲያኖች ተስፋ የምናደርገውና ክፉው የማይሰለጥንበት እውነተኛው ጌታ ብቻ የሚመራውና የሚያስተዳድረው ዓለም ስላለ ከመጪው ዓለም ለመለየት የአሁኑ ዓለም ብሏል::
በርግጥ የአሁኑ ዓለም ምንም
እንኳ በክፉ ቢያዝም በክርስቶስ ላሉት ግን የሥራ ቦታ ነው:: ስለዚህም ነው ሐዋርያው “በሥጋ መኖሬ ለእኔ የሥራ ፍሬ ቢሆን ምን
እንድመርጥ አላስታውቅም:: በእነዚህ በሁለቱ እጨነቃለሁ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፤ ከሁሉም ይልቅ እጅግ የሚሻል
ነውና:: ነገር ግን በሥጋ መኖሬ ስለ እናንተ እጅግ የሚያስፈልግ ነው:: ያለው:: ፊል 1፥22::
በአሁኑ ዓለም በሥጋ በመኖራችን
የመንፈስ ፍሬዎች እያፈራን ለሚድኑት የሕይወት ሽታ እንሆናለን:: ካዳነን ጌታ ጋርም እየኖርን በሕይወታችን እንሰብከዋለን:: በእርሱ
በወይኑ ግንዳችን ላይ ያለን ቅርንጫፎች እንደመሆናችን ከሕይወታችን (ከኑሯችን) የሚገኘው የወይንነታችን ፍሬ ለብዙዎች መዳን ምክንያት
ይሆናል:: የዳኑትንም ያጽናናል፣ ያበረታታል:: የእኛ በሥጋ መኖር ምንም እንኳ በኋላ ከክርስቶስ ጋር የሚኖረንን ኑሮ ባይደርስም
ለሌሎች ግን ብዙ ጥቅም ይሰጣል:: ለወንጌል መስፋፋት ለቤተክርስቲያን ዕድገትና ጽናት አስፈላጊ ነው:: የእግዚአብሔርን ሐሳብ የምናገለግልበት
ጊዜአችን ነውና:: አንድያ የእግዚአብሔር ልጅ ወደዚህ ዓለም የመጣበት ምክንያት እኛን ከዓለም ሊወስደን ሳይሆን ክፉው ዲያብሎስ
ካመጣብን ሞትና የኃጢአት ባርነት ነፃ አውጥቶን እንዲሁም በዚህ ዓለም በዲያብሎስ መሪነት ከሚሠራው ክፉ ሥራ ሁሉ በደሙ ከልሎ እስከ
ጊዜው ድረስ በዚሁ ዓለም ሊተወን ነው:: ጌታ ስለዚያም ነው በአገልግሎቱ ፍጻሜ በጸለየው ጸሎት ውስጥ “ከክፉ እንድትጠብቃቸው እንጂ ከዓለም እንድታወጣቸው አሌለምንም” ያለው፡፡ዮሐ 17፥15
የአሁኑ ዓለም ለዘላለማዊው
ኑሮአችን የምንዘጋጅበት ስንቅ የምናከማችበት ነው:: እንዲህ ባይሆን ኖሮ ራሳቸውን የሚገድሉ ሰዎች በፈጣሪ ፊት ሲቀርቡ ወቀሳና
ከሰሳ አይኖርባቸውም ነበር:: ይልቁንም ክፉው ከሆነው ዓለም ለመለየት በራሳቸው ላይ የወሰዱት እርምጃ የክብር አክሊል እንዲያገኙ
ያስችላቸው ነበር:: እግዚአብሔር ግን ራሳቸውን የሚያጠፉትን ይቀጣል:: “ማንም የእግዚአብሔርን ቤተመቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር
እርሱን ያፈርሰዋል” ተብሏል:: 1ቆሮ 3፥17:: በሌላ መልኩም ነፍሰ ገዳዮችም የክብር አክሊል ይሸለሙ ነበር:: የገደሏቸውን ሰዎች
ክፉ ከሆነው ከዚህ ዓለም በሞት እንዲለዩ አድርጓቸዋልና:: ሆኖም
ግን ክፉውን ዓለም ክፉ በመሥራት /በመግደልና በመሳሰሉት የተበላሹ ሥነምግባሮች/ ማሸነፍ ማምለጥ ስለማይቻል ነፍሰገዳዮችም ይቀጣሉ::
ክፉውን በክፉ ተቃውመዋልና::
ክፉ ማድረግ ተፈጥሯዊ ፍላጎታችን
ስላልሆነ በአሁኑ ዓለም ክፉ እያደረጉ የሚኖሩ ሁሉ ይቀጣሉ:: ሰው ሆኖ ከተፈጥሮአዊ ሂደቶችና ፍላጎቶች የሚያመልጥ ማንም የለም::
ለምሳሌ: መጸነስ፣ መወለድ፣ ማደግ፣ መብላት፣ መጠጣት፣ መተኛት፣ መነሣትና መሞት የመሳሰሉት በተፈጥሮ ሂደት ውስጥ የምንደርስባቸው ና የምናልፍባቸው ሂደቶችና ፍላጎቶች ናቸው::
እነዚህ በሰው ተፈጥሮ ውስጥ የግድ ይከናወናሉ:: ሁላችን ለእነዚህ ሂደቶችና ፍላጎቶች የተገዛን ነን:: ነገር ግን ክፉ መሥራት
እንዲህ ቢሆን ኖሮ ማንም ሊያስወግደው /ሊያመልጠው/ አይችልም ነበር:: ይህ ክፉ ዓለም ቢያንስ አንድ ንጹሕ ሰው አስተናግዷል::
ያም ንጹሕ ሰው ክርስቶስ ነው:: ደግሞ እርሱን እየመሰሉ የሚኖሩ ሁሉ ክፉ ከሆነው ሥራ ጋር ኅብረት የላቸውም:: ስለዚህ ክፉ አለማድረግ ይቻላል:: ተፈጥሮአዊ አይደለምና:: የማይቻል ቢሆን
ኖሮ “ክፉውን ነገር ተጸየፉት” “ከክፉ ሽሽ” ባልተባለም ነበር ሮሜ
12፥9፣ መዝ 36፥27::
ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ
ክርስቶስ ክፉ ከሆነው ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ እንደ አምላካችን
ና እንደ አባታችን ፈቃድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ::
ጌታ ራሱን የሰጠበት ምክንያት
ስለኃጢአታችን መስዋዕት ሆኖ ከዲያብሎስ አገዛዝ ሊያስለቅቀን /ነጻ ሊያወጣን/ ነው:: የክርስቶስን የማዳን ሥራ በተመለከተ የእግዚአብሔር
አብ ፈቃድና የኢየሱስ ሥራ ተጠቅሷል:: የአብ ፈቃድ ሲባል ሥላሴ በፈቃድ አንድ ቢሆኑም እግዚአብሔር ዓለምን ለማዳን ከዘላለም የነበረውን
ዕቅድ ለአብ ሰጥቶ መናገር አግባብ ስለሆነ ነው:: በሰው ልጅ ድኅነት ውስጥ አብ ያቅዳል ወልድ ይተገብራል፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ
የወልድን ተግባርና የሰውን ልጅ ያግባባል /ሰዎች የወልድ (ኢየሱስን) የማዳን ሥራ እንዲረዱት ያደርጋል:: የእውነት መንፈስ በመጣ
ጊዜ ስለ እኔ ይመሰክራል:: ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኋል፤ ሁሉን ያስተምራችኋል፤ እኔ የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” ተብሏልና::
ዮሐ 14፥26፣ 15፥26፣ 16፥3::
ኢየሱስ ስለኃጢአታችን ራሱን የሰጠው በፈቃዱ ነው:: ይህ የኢየሱስ ስለ እኛ
ኃጢአት ራሱን የመስጠት ፈቃድ የአብም ፈቃድ ነው:: በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር
አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዷልና ተብሏል ዮሐ 3፥16:: እንዲሁም “ልጅንም አይቶ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም
ሕይወት እንዲያገኝ የአባቴ ፈቃድ ይህ ነው” ይላል ዮሐ 6፥40:: አብ በፈቃዱ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ልጁን ለዓለም መድኃኒት
ይሆን ዘንድ ሰጠ:: ስለዚህ የክርስቶስ ፈቃድ የአብና የመንፈስ ቅዱስም ፈቃድ ነው:: በጌቴሴማኒ የታየውም ይኸው ነው፡፡ ማቴ
26፥39
ክርስቶስ ያድነን ዘንድ
ራሱን ሰጠ ሲል: ስለ ኃጢአታችን የከፈለው ዋጋ ምን ያህል ውድ መሆኑን ይገልጻል:: ለኃጢአት ዋጋ ከፍሎ ኃጢአተኞችን ነጻ ማውጣት
በክርስቶስ አንድ ጊዜ የተከናወነ የመስዋዕትነት ሥራ ነው:: “ክርስቶስ ስለኃጢአታችን ሞተ በሦስተኛውም ቀን ተነሣ” ይላል::
1ቆሮ 15፥3-4:: እንዲሁም “ኃጢአተኞችን ሊያድን ክርስቶስ ኢየሱስ ወደ ዓለም መጣ” ይላል 1ጢሞ 1፥15:: ኢየሱስ ክርስቶስ
ለመስቀል ሞት ራሱን አሳልፎ የሰጠው ኃጢአተኞችን ከኃጢአት ባርነት ነፃ ለማውጣት ነው:: እርሱ በሰራው የማዳን ሥራም የባሕርይ አባቱ አባታችን ሆኗል፡፡ እርሱም በሥጋና በደም ከእኛ ጋር
ተካፍሏልና ወንድማችን ሆኗል፡፡ ስለዚህም አንድ ቤተሰብ ነን፡፡
ለአብ ከዘላለም እስከ ዘላለም ክብር ይሁን! አሜን::
በሌሎቹ የሐዋርያው መልዕክቶች
ውስጥ መጀመሪያ ላይ አሜን የሚለውን ቃል አናገኘውም:: ሐዋርያው
በዚህ መልዕክት መጀመሪያ ላይ አሜን የሚለውን ቃል መጠቀሙ አዲስና
ያልተለመደ አቀራረቡ ነው:: የተጠቀመበትም ምክንያት አስቀድሞ የክርስትና ማዕከልና ማኅተም ስለሆነው ስለክርስቶስ የመስቀል ሞትና
ትንሣኤ በዚህም ስለተገኘው ድኅነት ይህ ድኅነት ላመኑ ሁሉ የዘላለም ዋስትና መሆኑን እንዲሁም የአምላካችንንና የአባታችን የእግዚአብሔር
ፈቃድ በክርስቶስ መከናወኑን ወልድ /ኢየሱስ/ በፈቃዱ ራሱን የኃጢአታችን
መስዋዕት አድርጎ በማቅረቡ የተትረፈረፈ ጸጋና ሰላም እንደተሰጠን ዘርዝሯል:: የገላትያ ክርስቲያኖች በመግቢያው ላይ የተዘረዘረው
ሐዋርያዊ መልዕክትና ጸሎት በቂ መሆኑን እንዲረዱ እግዚአብሔር አብን ያመሰግንና አሜን ብሏል::
ጸጋ ይብዛላችሁ
No comments:
Post a Comment