Monday, May 27, 2013

የሐዋርያው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት ወደገላትያ ሰዎች ትንታኔው

የሐዋው የቅዱስ ጳውሎስ መልዕክት  ወደገላትያ ሰዎች ትንታኔ
የትንታኔው ዓላማ ፡ እግዚአብሔር  በዚህ መልዕክት ውስጥ ያስቀመጠልንን መለኮታዊ አሳቡን መረዳት ሲሆን ይህም ክርስቶስ ኢየሱስን በማመን ስለሚገኘው ድኅነትና ጽድቅ እንዲሁም  የክርስትናን ሕይወት እንዴት መኖር እንደሚገባ ማሳየት ነው፡፡
መግቢያ
የመልዕክቱ ጸሐፊ
የገላትያ  መልዕክት ጸሐፊ ሐዋርያው ጳውሎስ መሆኑን ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት ይስማማሉ፡፡
ሐዋርያው ጳውሎስ ማን ነው ?
በዚህ ስም ከመታወቁ በፊ ሳውል በመባል ይጠራ የነበረና  በአሕዛብ ምድር የሮም ግዛት በሆነችው በኪልቂያ ጠርሴስ ከቢንያም ነገድ የተወለደ አይሁዳዊ ነበር፡፡ ምንም እንኳ በዚያን ዘመን እንደዛሬው አሜሪካዊነት ሮማዊነት በቀላሉ የማይገኝ ቢሆንም  በሮም ግዛት መወለዱ ሮማዊ ዘግነት እንዲኖረው  አስችሎታል፡፡ ሐዋ 21፥39, 22፥22_29
ጳውሎስ በአሕዛብ ምድር ቢወለድም እድገቱ በአይሁድ ሕግና ሥርዓት መሠረት በታላቁ የብሉይ ኪዳን /የኦሪት ሕግ/ ምሁር እጅግ በተከበረው በገማልያል የኦሪትን መጻሕፍትና የአባቶቹን ወግ ጠንቅቆ እየተማረ ነበር፡፡ ሐዋ 22፥3, 5፥33_ 39 ለአባቶቹም ወግ ቀናተኛና በዘመኑ ከነበሩት የእምነት ክፍሎች ውስጥ ፈሪሳዊ ነበር፡፡ ከዚህም የተነሣ በክርስቶንስ  ያመኑትን ክርስቲያኖች የሚያሳድድና የሚያንገላታ  አደገኛ የቤተክርስቲያን ጠላት ነበር፡፡ እርሱም ስለራሱ ሲናገር “ በስምንተኛው ቀን የተገረዝሁ ከእስራኤል ትውልድ ከቢንያም ወገን ከዕብራውያን ዕብራዊ ነኝ ስለሕግ ብትጠይቁ ፈሪሳዊ ነበርሁ፡፡ ስለቅናት ብትጠይቁ ቤተክርስቲያንን አሳዳጅ ነበርሁ፡፡ በሕግ ስለሚገኝ ጽድቅ ብትጠይቁ ያለነቀፋ ነበርሁ” ይላል፡፡ ፊል 3፥5_7 ፣ ገላ 1፥13
ይሁን እንጂ በውስጡ የነበረውን ቅንነትና ታማኝነት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ተሰማርቶ እየተጠቀመበት ስለነበረ በደማስቆ ጎዳና ላይ በብርሃን ነጸብራቅ ጥሪ ተላለፈለት፡፡ በእግዚአብሔር ፈቃድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ተመርጦ በራሱ በኢየሱስ ጥሪው ተላለፈለት፡፡ ጌታ ኢየሱስ በአገልግሎት ዘመኑ  የቀደሙትን ሐዋርያት ለሥራ የተሰማሩበት ቦታ ድረስ እየሄደ ከጠራቸው በኋላ”እኔ መረጥኋችሁ” እንዳላቸው ሁሉ፤ አሁንም ከትንሥኤውና ከዕርገቱ በኋላ ሳውልን ለአገልግሎት ጠራው፡፡ አስቀድሞ ከነበረው አፍራሽ  ዓላማው አንጻር ይህ ታላቅና የጌታ የምህረቱ መገለጫ የሆነው ጥሪ ደርሶት ምስጋና ሲያቀርብ “ለአገልግሎት ሾሞኝ ታማኝ አድርጎ ስለቆጠረኝ ኃይል የሰጠኝን ክርስቶስ ኢየሱስን ጌታችንን አመሰግናለሁ” ካለ በኋላ የራሱን ሕይወት ሲተርክ”አስቀድሞ ተሳዳቢና አሳዳጅ አንገላችም ምንም ብሆን ይህን አደረገልኝ ነገር ግን ሳላውቅ ባለማመን ስላደረግሁት ምሕረትን አገኘሁ” ብሏል፡፡1ጢሞ 1፥12_13፡፡



ሳውል  ከአይሁዳዊነት ወደ ክርስትና የተመለሰበትን መንገድ ስናስተውል ብዙ ኃጢአት ባለበት የእግዚአብሔር ምህረት ምን ያህል እንደሚበዛ ያስገነዝበናል፡፡ሳውል የሚፈጥነው ለማጥፋትና ለመጥፋት ነበር፡፡ አንድ አዳኝ ለአደን ወጥቶ የሚፈልገውን አውሬ ከርቀት ከተመለከተ በኋላ ጦሩን ሰብቆ  ቀስቱን ቀስቶ ዒላማ ውስጥ እስከሚገባለት ድረስ እንደሚጠብቅ ሁሉ ጌታ ኢየሱስም ሳውል የሚድንበትንና  ያን ለአመጽ ይበረታ የነበረ ኃይሉን፣ቅናቱንና ዕምነቱን ለተሻለ ጥቅም የሚያውልበትን ጊዜ፣ቦታና ሁኔታ ነበር የሚጠብቀው፡፡ ሳውል ከሊቀ ካህናቱ የተቀበለው ደብዳቤ ሌሎችን ለማሳደድና ለመግደል የነበረውን ሥልጣን የሚገልጽ ቢሆንም ራሱን ከሚገጥመው መከራ የሚታደገው ግን አልነበረም፡፡ የማያስተውል ሰው ያለውን ዕውቀት፣ኃይልና ልምድ ከዲያብሎስ ጋር በመተባበር ለጥፋት ያውለዋል ፡፡ እጠፋለሁ ብሎ ግን አያስብም፡፡ “የእግዚአብሔር ኃይል ግን ለማዳን “ነው፡፡ ጌታ ኢየሱስ የሚጠብቀው ሰዓት በደረሰ ጊዜ ለማዳን በሚገለጠው በእግዚአብሔርነቱ ኃይል በአሕዛብና በነገሥታት እንዲሁም በእስራኤል ልጆች ፊት ስሙን ይሸከምና የድኅነት አዋጅ ነጋሪ ይሆን ዘንድ ሳውልን አሸነፈው፡፡ ከሰማይ መለኮታዊው ብርሃን ሲያንጸባርቅበት ይረግጣት በነበረው መሬት ላይ ወደቀ፡፡ ሌላውን ከማስደንገጥና ጣዕረ ሞት በመሆን ከማስፈራራት በስጠቀር አይደነግጥ አይፈራ  የነበረው ሳውል በድንጋጤና በፍርሃት ነፍሱ ተጨነቀች፡፡ የሚጠራውን ማየት አልቻለም፡፡ ለክርስትና በነበረው ጥላቻ ዓይኑ ታውሮ ነበርና፡፡ እጁም በእነ ሰማዕቱ እስጢፋኖስ ደም የተነከረ ስለነበረ ሰውነቱ እየተብረከረከ መቆም ተሳነው፡፡ ለነገሩ አለማመኑ ሳያንስ የሰው ደም ያሰከረው ምን ጤና አለው፡፡ በኃይሉ ያሸነፈው ጌታ በፍቅሩ አዳነው፡፡
ዛሬም በጥላቻ ዓይኑ የታወረበት ከማመን ልቡ የዘገየ ማንም ቢኖር ሕይወቱ ኑሮው ሁሉ እየተናጋና እየተናጠ በፍርሃትና በሰላም እጦት መሰቃየቱ የማይቀር ነው፡፡ “ለክፉዎች ሰላም የላቸውም” ተብሏልና፡፡ ለእኛ ቅን መስሎ የታየን መንገድ ሁሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ የሚፈጸምበት ዓላማው የሚከናወንበት ላይሆን ይችላል፡፡ አስቀድሞ መንገድን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ አይሁድ የጌታን ደቀመዛሙርት በሸንጎ ፊት አቁመው “ኢየሱስ” በሚለው ስም እንዳያስተምሩ ሲያዟቸውና ሊገድሉአቸውም ሲመክሩባቸው፤  ታላቁ የከበረው የሕግ መምህር ገማልያል ከመካከላቸው ተነስቶ “ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደሆነ ይጠፋልና  ከእግዚአብሔር እንደሆነ ግን ታጠፉአቸው ዘንድ አይቻላችሁም  በእርግጥ ከእግዚአብሔር ጋር ስትጣሉ ምናልባት እንዳትገኙ” አላቸው፡፡ ሐዋ 5፥38፡፡ለነገሩ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ኢየሱስ በተባለው ስም ምክንያት ከሚገጥም ነቀፌታና መከራ ማምለጥ የቻለው ተፈጥሮው ረቂቅ ስለሆነና ስለዚህ ስም ተገልጦ የተነጋገረውም ከእመቤታችን ከድንግል ማርያምና ከዮሴፍ ጋር ብቻ ስለነበረ ነው፡፡ከወለደችው ከድንግል ማርያም ጀምሮ ኢየሱስ የሚለው ስም ባለቤት የሆነው ራሱ ኢየሱስና እርሱን ያመኑና የተከተሉት ሁሉ በስሙ ምክንያት የሚመጣው መከራ ተካፋዮች ሆነናል፡፡ ሉቃ 1፥26_38፣ማቴ 1፥21 ፣ ማቴ 5፥11_ 13፣ፊል 1 ፥29፡፡ እግዚአብሔር ከላከውና የእግዚአብሔርን ፈቃድ ከሚያውጅ ጋር መጣላት ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ነው፡፡ ጌታችንም  ለሳውል ጥያቄውን ሲያቀርብ“ ሳውል ሳውል ስለምን ታሳድደኛለህ?” የሚልነበር፡፡ ሐዋ 9፥4 ባለችን ጥቂት ዘመን ከእግዚአብሔር ጋር  ተስማምተን ለመኖር ከሳሽ ወቃሽና አሳዳጅ የሆነ ልብ እንዳይኖረን ያስፈልጋል፡፡
እንግዲህ በብሉይ ኪዳን ዘመን ሙሴን በተራራ ላይ ለአርባ ቀንና ሌሊት አቆይቶ በእሳት አምድ ሆኖ ያስተማረ አምላክ የአዲስ ኪዳንን የአርነት/ነጻነት/ ወንጌል ለሳውል ለማስተማር ያን ያህል ቀን አላስፈለገውም፡፡ ይልቁንም በውስጡ ተከማችቶ ከኖረው ከብሉይ ኪዳን አስተምህሮ ውስጥ ልዩ በሆነ መለኮታዊ አሠራር በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነውን የአዲስ ኪዳንን አጠቃላይ መለኮታዊ እሳቤና ሥራ ይገባው ዘንድ ከዓይኑ ላይ ቅርፊቱ እንዲወድቅለት አደረገ፡፡ሐዋ 9፥1_21፡፡ ሳውልም  በአዲስ ኪዳን በክርስቶስ የተፈጸመው መዳን ግልጽ ሲሆንለት ወዲያው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ  እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ  በየምኩራቦቹ መስበክ ጀመረ፡፡የሳውል የአዲስ ኪዳን እውቀት መገለጥ ነው እንጂ ትምህርት አይደለም፡፡  ስለዚህም ነበር ለገላትያ ቤተክርስቲያን መልእክቱን ሲጽፍ” በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልኁትም አልተማርሁትምም” ያለው፡፡ ገላ 1፥11 ከጌታ ተምሯልና ያሳድደው ስለነበረው መመስከርና መሰደድ ጀመረ፡፡
በሐዋርያት ሥራ እንደተገለጸው በአንጾክያ በነበረችው ቤተክርስቲያን የነበሩት መምህራንና ነቢያት በጾምና በጸሎት ሆነው ጌታን እያመለኩ በነበሩበት ጊዜ  መንፈስ ቅዱስ ሳዉልንና በርናባስን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ አለ፡፡ በዚያ የነበሩትም ከጾሙ ከጸለዩ በኋላ እጃቸውን ጭነው አሰናበቱአቸው፡፡ ከዚህ ሰዓት ጀምሮ ሳውል የሚለው ስም ተለውጦ ጳውሎስ ሲባል እናገኛለን፡፡ ሐዋ 13
ቅዱስ ጳውሎስ በአገልግሎቱ ሦስት ሐዋርያዊ ጉዞዎችን አካሂዷል፡፡ አስራ አራት መልእክታትን ጽፏል፡፡ በአገልግሎቱም ፍጻሜ ስለክርስቶስ ተሰውቷል፡፡ በረከቱ ይደርብን

ጸጋ ይብዛላችሁ !!!


No comments:

Post a Comment