ምዕራፍ 1፥1-3
“በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባስነሳው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ ከእኔም ጋር ያሉት ወንድሞች ሁሉ ወደ ገላትያ አብያተክርስቲያናት”
ክፍል ፩
ከቅዱስ ጳውሎስ መልዕክታት ውስጥ በኃይል የተጀመረና እስከ ፍጻሜውም ድረስ ጠንካራ የአዲስ ኪዳን ትምህርተ መለኮት ያለበት መልዕክት ወደ ገላትያ የላከው መልዕክት ነው:: ኃይለኛነት የጠላት ወይም የምንደኛ እረኛ ጠባይ ቢሆንም ሁልጊዜ በጨዋነትና በተረጋጋ ሁኔታ ደቀ መዛሙርትን ማስተማር ግን አግባብ አይደለም:: ተግሳጽን የያዘ ሊያርም የሚችል የኃይል ንግግር የሚያስፈልጋቸው ጊዜ አለና:: ጌታ ኢየሱስ ደግና አዛኝ ሆኖ ሳለ ደቀ መዛሙርቱን አንዳንድ ጊዜ በበረከት ቃል ሲናገራቸው ሌላ ጊዜ ደግሞ በኃይለ ቃል ይናገራቸው ነበረ:: ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ፊልጶስ ቂሣርያ በደረሱ ጊዜ ለደቀ መዛሙርቱ አንድ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር:: የእጁን ታምራት ሲያዩ የቃሉን ትምህርት ሲሰሙ አብረውት ከመዋልና ከማደራቸው አንጻር መረዳታቸውን እንዲረዱ መጠየቅ ነበረባቸው:: ጌታ ኢየሱስም “ሰዎች የሰውን ልጅ ማን እንደሆነ ይሉታል?” አለና ሌሎች ሰዎች ስለእርሱ ያላቸውን ግንዛቤ ከደቀመዛሙርቱ ለመስማት ጠየቀ:: እነርሱም የሰሙትን አሰሙት::
ጥያቄው ቀጠለ “እናንተስ እኔን ማን እንደሆንሁ ትላላችሁ?” አላቸው:: ዝምታ ሰፈነ:: ሁሉም ምላሽ ለማግኘት ወደ ልቡናው ጓዳ ገባ:: እያንዳንዱም በሐሳቡ በራሱ ልብ ውስጥ ይሯሯጥ ጀመር:: እነርሱ ጥያቄውን ከአፉ ሳይጨርስ መልሱን መስጠት ነበረባቸው:: ነገር ግን ስለ ኢየሱስ ለመናገር መረጃ ከሰማይ ካልተለቀቀ በስተቀር ብልጭታን ያህል መረዳት ማገኘት ከባድ ነው:: ስለዚህም ደቀ መዛሙርቱ እርስ በእርስ ለመተያየት ወይም ወደ ኢየሱስ የመመልከቻም ጊዜ አልነበራቸውም:: ሁሉም ውስጣቸው ገብተው ተደበቁ::
ይገርማል! ጌታ ግን አሳብን የሚያነብ በልብ ውስጥ የሚመላለሰውን ምኞት የሚያደምጥ እንደመሆኑ ፈጣን ምላሽ ባለመስጠታቸው ሊነቅፋቸው አልወደደም:: ጠበቃቸው:: ዝምታው በሰፈነበት ሰዓት ጴጥሮስ ለካ በአካል እንጂ በመንፈስ መካከላቸው አልነበረም:: ስለ እርሱ በብቃት የሚገልጽለትን መንፈስ ቅዱስን ለማስተናገድ ልቡናውን እያዘጋጀ ነበር:: ከጥቂት ቆይታዎች በኋላ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” የሚል ድምጽ ከጴጥሮስ ወጣ:: አይደለም ሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ራሱ ጴጥሮስም ሳይደነግጥ አልቀረም::
አስቀድሞስ ጌታ “የምትናገሩት በዚያች ሰዓት ይሰጣችኋልና እንዴት ወይስ ምን እንድትናገሩ አትጨነቁ በእናንተ የሚናገር የአባታችሁ መንፈስ ነው እንጂ የምትናገሩ እናንተ አይደላችሁም” ብሏቸው አልነበር ? ማቴ 10፥19:: ሁሉም ግን ይህን አላሰቡም ነበር:: ጴጥሮስ ግን ተሣካለት:: ጌታም አስቀድሞ በዮርዳኖስ ስለልጁ የመሰከረ አብ አሁንም በጴጥሮስ ሆኖ እየተናገረ መሆኑን ስላወቀ “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይህን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ” አክሎም “በዚህችም ዓለት ላይ ቤተክርስቲያኔን እሠራለሁ” አለው:: ዓለት ያላት “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” የምትለውን እምነት ነው፡፡ ማቴ 16፥16-18::
ጌታ ኢየሱስ በአንድ ሥፍራ “ብፁዕ” ብሎ የባረከውን ጴጥሮስን ወዲያውኑ እርሱ ወደ ኢየሩሳሌም እንደሚወጣና በዚያም ብዙ መከራ ደርሶበት እንደሚሞት በሦስተኛው ቀን እንደሚነሣ ለደቀመዛሙርቱ ሲገልጥላቸው ጴጥሮስ “አይሁንብህ ጌታ ሆይ ይህ ከቶ አይደርስብህም ብሎ ሊገስጸው ጀመር” ጌታም “ወደ ኋላ ሂድ አንተ ሰይጣን የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና እንቅፋት ሆነህብኛል” ብሎታል ማቴ 16፥22-23:: አንድ እረኛ /መምህር/ መልካም የሚባለው ተገቢውን ነገር በተገቢው ጊዜና ቦታ መናገር ሲችል ነው:: ጌታ ደግሞ ቸር እረኛ ፣ደግ እረኛ ነው:: ነገ ኃላፊነት የሚቀበሉት ደቀ መዛሙርቱ በሰውኛ ስሜትና አመለካከት ተይዘው የእግዚአብሔርን ሐሳብ ሳያገለግሉ እንዳይቀሩ ይፈልጋል:: ስለዚህ ጴጥሮስን የሰይጣን አሳብ አስተናጋጅ ሆኖ ሲያገኘው ገሰጸው:: በሌላ ጊዜ ደግሞ ደቀ መዛሙርቱ ጌታ ባቀረበው ምሳሌ ግራ ተጋብተው ስለነበረ ጴጥሮስ ወደ ጌታ ጠጋ ብሎ “ጌታ ሆይ ምሳሌውን ተርጉምልን” ሲለው ጌታ ኢየሱስም መልሶ “እናንተ ደግሞ እስከ አሁን የማታስተውሉ ናችሁን?” አላቸው:: ማቴ 15፥16:: እነዚህ የግሳጼ ንግግሮች ማስጠንቀቂያ ሆኗቸው ጌታችን በያዕቆብ ጉድጓድ አጠገብ ከሰማርያዊቱ ሴት ጋር ሲነጋገር አይተው አንዳች ለመናገር አልደፈሩም ነበር:: ዮሐ 4፥27::
ቅዱስ ጳውሎስም የገላትያ ቤተክርስቲያንን በመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጉዞው የመሠረታት ናት፡፡ እርሱ ያስተማረውን ወንጌል የሚበክል ኑፋቄ ማኅበረ ክርስቲያኑን እየፈተነ መሆኑን ሲረዳና የእርሱንም ሐዋርያነት እየተጠራጠሩ መሆናቸውን ስላወቀ የገላትያን ምዕመናን “የማታስተውሉ የገላትያ ሰዎች” እያለ ይገስጻቸዋል:: እንደ ቆሮንቶስ ክርስቲያኖች እንኳ “ምን ትወዳላችሁ? በበትር ወይስ በፍቅር በየዋሃት መንፈስ ልምጣባችሁን?” እያለ ምርጫ ሊሰጣቸው አልፈቀደም:: ገላ 3፥3፣ 1ቆሮ 5፥17:: ይሁን እንጂ በግሳጼ ቃል አስደንግጦ ብቻ ዝም ማለቱ አግባብ ስላልሆነ “ልጆቼ ሆይ ክርስቶስ በእናንተ እስኪሳል ድረስ ዳግመኛ ስለ እናንተ ምጥ ይዞኛል” እያለ በየእኔነት ልብ ሲያረጋጋቸው ይስተዋላል:: ገላ 4፥19::
እንግዲህ ይህ መልዕክት ሐዋርያው በቁጣ መንፈስ ሆኖ የጻፈው መልዕክት ነው:: ቃሉም የሚለው “ተቆጡ ኃጢአትን አታድርጉ” ነውና:: ኤፌ 4፥26:: መቆጣቱ ተገቢ አልነበረም የሚል ካለም የገላትያ ክርስቲያኖች የመጀመሪያው ሐዋርያዊ ጉዞው ፍሬ እንደመሆናቸው መጠን ሐዋርያው መቆጣቱ ብዙ አያስደንቅም:: ምክንያቱም እንኳን ወንጌልን ለማስረዳት ብዙ የተለፋበት ሕዝብ ይቅርና አንድ ቀን አገልግሎት የተሰጠው ሰውም እንኳ ቢሆን ሲጠፋ ያሳዝናልና ነው::
በገላትያ ቤተክርስቲያን የተከሰተው ችግር እንደ ዋዛ ታይቶ የሚታለፍ አልነበረም:: አንዳንድ ነጭናጫ በትንሽ በትልቁ የሚቆጡ ግልፍተኛ ሰዎች በትንሽ ችግር ብዙ ሊቆጡ ይችላሉ:: እነርሱ ሰነፍ ስለሆኑና ሥራዎቻቸውን በፍጥነት መሥራት ስለማይችሉ በዚያው መጠን ጥቂት የሠሩትን ሰዎች ያበላሹባቸው ሲመስላቸው ይበሳጫሉ:: ኃይለ ቃልም ይናገራሉ:: ጳውሎስ ግን እንደነርሱ አይደለም:: ታዲያ ሐዋርያውን ያስቆጣው ምንድን ነው? የተፈጠረው ችግር ከባድና እጅግ ሊታሰብበት የሚገባ ባይሆን ኖሮ የሐዋርያው ቁጣ በጣም አስፈላጊ አለመሆኑን ራሱ ስለሚረዳ አያደርገውም ነበር:: በገላትያ ቤተክርስቲያን የተፈጠረው ችግር ግን ከባድ ነበር:: እርሱ አስተምሮአቸው በክርስቶስ ያመኑትንና በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቁትን ክርስቲያኖች ከክርስቶስ የሚለይና የሚነጥል አስተምህሮ የሚያስተምሩ ሐሰተኛ ወንድሞች በመካከላቸው ገብተው የሐሰት ትምህርታቸውን ማስተማር ጀምረው ነበር:: ትምህርታቸውም ሁለት መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ያነጣጠረ ነበር ::
1. በጸጋ በተገኘውን ድኅነት
2. በጳውሎስ ሐዋርያነት
እነዚህ ሐሰተኛ መምህራን ከንቱ ውዳሴን በመፈለግ የሰከሩና በአይሁድ ሥርዓት ልባቸው የተማረከ ስለነበር በክርስቶስ ያመኑና በሥላሴ ስም የተጠመቁ ክርስቲያኖች እንደ ሙሴ ሥርዓት ግዝረትን መፈጸም አለባቸው:: አለበለዚያ ግን ድኅነታቸው ሙሉ አይደለም እያሉ ያስተምሩ ነበር:: በመቀጠልም ጳውሎስ ትክክለኛ ሐዋርያ አይደለም ጴጥሮስ ፣ዮሐንስና ሌሎቹም ሐዋርያት ይበልጡታል፤ እርሱ አንድ ነው፡፡ እነርሱ ግን ብዙ ናቸው፡፡ ደግሞም እነርሱ የቤተክርስቲያን አዕማድም ናቸው፡፡ ሐዋርያነትንም የተቀበሉት በቀጥታ ከኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ገላ 2፥9 እርሱን ሐዋርያ ብለው የሾሙት ግን እነ ጴጥሮስ ናቸው እያሉ የእርሱን አገልግሎትና አገልጋይነት ውድቅ ለማድረግ ይጥሩ ነበር:: ደግሞም በክርስቶስ ያመኑ ክርስቲያኖች ሕገ ኦሪትን እንዳይፈጽሙ የክርስቶስ ተከታዮች የሆኑት ዋኖቹ ሐዋርያት አልከለከሉም፡፡ እርሱ ግን ይከለክላል ይሉ ነበር፡፡ ምናልባት እነ ጴጥሮስ ወንጌል ያለኦሪት ጥምቀት ያለ ግዝረት አታድንም የሚሉትን አይሁድ ክርስቲያን በግልጽ ያልተቃወሙአቸው የአይሁድን ድካም ስለሚያውቁ እንጂ በእነርሱ ሐሳብ ተስማምተው አይሆንም ፡፡ አስቀድመው የያዙትን እንዲለቅቁ በመታገል ጊዜ ከመፍጀት መድህን የሆነውን ጌታ ኢየሱስን እንዲያምኑና እንዲጠመቁ አበክሮ ማስተማሩ የበለጠ ትርፋማ ስለሚያደርግም ነው፡፡ ለምሳሌም ያህል ጴጥሮስ ሦስት ሺህ እና አምስት ሺህ አማኞች ለክርስቶስ መንግሥት በማረከበት አገልግሎት ስለዚህ ጉዳይ ምንም ያለው ነገር አልነበረም፡፡ሐዋ 2፥14-47፣4፥4፡፡ በመጀመሪያውም ሲኖዶስ ስብሰባ ላይ የተላለፈው ውሳኔ ከአህዛብ ወደ ክርስትና የሚገቡትን የሚመለከት ነበር እንጂ ከአይሁድነት ወደ ክርስትና የሚገቡትን የሚመለከት ነገር በግልጽ አልተቀመጠም፡፡ ሆኖም ከአሕዛብነት ወደ ክርስትና ለሚገቡት አማኞች የተላለፈው ውሳኔ ከአይሁድነት ወደ ክርስትና ለሚገቡት የማይሰራበት ምክንያት አይኖርም፡፡ሐዋ 15፥22-29
ለዚህ ሲኖዶስ ስብሰባ ምክንያት የነበረው ከይሁዲነት ወደ ክርስትና የገቡ ክርስቲያኖች ከአህዛብነት ወደ ክርስትና የሚገቡትን ሰዎች መገረዝና ሕግን መጠበቅ እንዳለባቸው እየተናገሩ ያውኩአቸው ስለነበረ መፍትሔ ለመስጠት ነበር ፡፡ወንጌል ያለ ኦሪት ጥምቀት ያለ ግዝረት አያድንም የሚለውን ሐሳብ ሐዋርያት ሲገልጹት “ሸክም፣ጭነት” ብለው ነው፡፡ሐዋ 15፥29፡፡ በርግጥ ይህ ሐሳብ የሐዋርያት ብቻ ሳይሆን የመንፈስ ቅዱስም ነው፡፡ ይህንን ሐሳብ ይዘው የሚያራምዱትን ሰዎች ሐዋርያት ሲገልጹአቸው “ ሳይላኩ ተልከናል ባዮች፣ያልታዘዙ ሰዎች፣ከእኛ ዘንድ የወጡ ነገር ግን ከእኛ ጋር ያልነበሩ፣ልብን የሚያውኩና በቃል የሚያናውጡ” በማለት ነበር፡፡ ሐዋ 15፥24_25
ጳውሎስ የአሕዛብ ሐዋርያ ስለሆነ ይህ የኑፋቄ አስተሳሰብ ወደ ክርስትናው የሚመጡትን አማኞች የበለጠ እንደሚፈትናቸው ያውቃል፡፡ ሆኖም ግን ወንጌል ያለ ኦሪት ጥምቀት ያለግዝረት አያድንም ባዮችንና በዚህ የኑፋቄ ሐሳብ የተጠለፉትን አማኞች “እነኾ እኔ ጳውሎስ እላችኋለሁ ብትገረዙ ክርስቶስ ምንም አይጠቅማችሁም” ደግሞም “በሕግ ልትጸድቁ የምትፈልጉ ከክርስቶስ ተለይታችሁ ከጸጋው ወድቃችኋል” ብሏቸዋል፡፡ ገላ4፥2,4 በገላትያ ቤተክርስቲያን የገባው የሐሰት ትምህርት በምዕመናን ተቀጣጥሎ በዕድገት ላይ የነበረችውን ቤተክርስቲያን ሊያፈርሳት በይሁዲነት መንፈስ ሊያጥለቀልቃት ተቃርቦ ነበር። ሐዋርያው በሐዘንና በቁጣ ተመልቶ “ስለ እናንተ አመነታለሁና አሁን በእናንተ ዘንድ ኾኜ ድምጼን ልለውጥ በወደድሁ” ይላቸዋል፡፡ ገላ 4፥20
ደግሞም የእርሱን ሐዋርያነት እየነቀፉ ለነበሩትም ”በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታንም ባስነሳው በእግዚአብሔር አብ ሐዋርያ የሆነ እንጂ ከሰዎች ወይም በሰው ያልሆነ ጳውሎስ “ እያለ የእርሱ የሐዋርያነት ሥልጣን ከእግዚአብሔር የተሰጠው መሆኑን ያስረዳል፡፡ ከሰዎች ሲል ሰዎች ተሰብስበው በጋራ መሻታቸው ተስማምተው የመረጡት አለመሆኑን ሲገልጽ ፤ በሰው ሲል ደግሞ በእግዚአብሔር ፈቃድ ተመርጦ ሥርዓተ ሹመቱ በሰው የተከናወነ አለመሆኑን ያስረዳል፡፡
ጳውሎስ በደማስቆ ሰማያዊውን ጥሪ ከተከቀበለ በኋላ በቀጥታ ወደ ሐናንያ ዘንድ ሄዶ ተጠምቋል:: ሐናንያ አጥማቂው እንጂ ከነበረበት የጥፋት መንገድ የመለሰውና ያሰመነው አአይደለም :: ሐዋ 9፥10-18:: ከሰማይ ከተለቀቀው የብርሃን ነጸብራቅ ውስጥ የጠራው ክርስቶስ ራሱ ነው:: ጌታ ኢየሱስ አስቀድሞ በምድራዊ ዘመኑ ባሕር ዳር መረባቸውን በማዘጋጀት ላይ የነበሩትን ወንድማማቾች ያዕቆብንና ዮሐንስን እንዲሁም ጴጥሮስንና እንድርያስን የጠራቸው እርሱ ነው:: ለሦስት ዓመታት ያህል አብረውት ሆነው እንዲማሩ ካደረገ በኋላ ማስተማር፣ አጋንንት ማውጣት፣ ደዌ መፈወስ የሚችሉበትን ሥልጣን ሰጥቷቸዋል:: ጳውሎስንም “ሳውል ሳውል ለምን ታሳድደኛለህ? አንተ የምታሳድደኝ እኔ ኢየሱስ ነኝ የመውጊያውን ብረት ብትቃወም ላንተ ይብስብሃል!” በማለት የጠራውና ያስጠነቀቀው እርሱ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው፡፡ ለአጥማቂው ሐናንያም ደግሞ “ይህ በአሕዛብ በነገሥታትም፣ በእስራኤል ልጆች ፊት ስሜን ይሸከም ዘንድ ለእኔ የተመረጠ ዕቃ ነውና ሂድ ስለ ስሜ ስንት መከራ ሊቀበል እንዲያስፈልገው እኔ አመለክተዋለሁ” ብሎ ነግሮታል:: ሐዋ 9፥4-6፣ 14-16::
እንግዲህ የቀደሙትን ሐዋርያት ለሦስት ዓመት ያስተማራቸው ጌታ ጳውሎስን ለማስተማር ረጅም ጊዜ አላስፈለገውም:: በአሕዛብ፣ በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት ስሜን ይሸከማል ብሏልና ለምስክርነት ብቁ የሚያደርገውን ትምህርትና ጸጋ ሰጥቶታል:: ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ብዙ ፈላስፎችና በጥበባቸው ዘመናቸውን ያስደመሙ፤ ከነገሥታትና መኳንንት ወገንም በብዙ ኃይላቸውና ሥልጣናቸው የሚመኩትን እንዲሁም በሙሴ ሕግ አእምሮአቸው የታሰረባቸውን አይሁድንም በወንጌል ማሸነፍ የቻለው ከክርስቶስ የተማረና ጸጋውንም የተቀበለ በመሆኑ ነው:: በመልዕክቱም “ወንድሞች ሆይ በእኔ የተሰበከ ወንጌል እንደ ሰው እንዳይደለ አስታውቃችኋለሁ ኢየሱስ ክርስቶስ ገልጦልኛል እንጂ እኔ ከሰው አልተቀበልሁትም፤ አልተማርሁትምም” ብሏል ገላ1፥11 :: ጸጋውንም በተመለከተ “ሐዋርያ ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ ነገር ግን በእግዚአብሔር ጸጋ የሆንሁ እኔ ነኝ፤ ለእኔም የተሰጠኝ ጸጋው ከንቱ አልነበረም” ይላል 1ቆሮ 15፥9-10 እንደተጠመቀም በቀጥታ ወደ አገልግሎቱ ነበር የገባው::
ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ በየሙክራቦቹ እየሰበከ አይሁድ አንዳች መናገር እንዳይችሉ አድርጎ ያስረዳቸው ነበር:: እነርሱ ግን ያላቸው ብቸኛ ችሎታ መግደል ስለነበር ይገድሉት ዘንድ መማከር ጀመሩ:: ሐዋ 9፥20-25:: ስለክርስቶስና ስለወንጌል የደረሰበትን መከራ ከሌሎቹ ጋር አነጻጽሮ ሲናገር “ከሁላችው ይልቅ ግን ደከምሁ ዳሩ ግን ከእኔ ጋር ያለው የእግዚአብሔር ጸጋ ነው እንጂ እኔ አይደለሁም” ይላል 1ቆሮ 15፥10:: እንዲህ የሚለው በሌሎቹ ሐዋርያት ላይ የበላይነት ለመያዝ ሳይሆን አገልግሎቱንና ሐዋርያነቱን የሚነቅፉ ሰዎች እንዲታረሙ ነው::
ጳውሎስ “በሰዎች . . . ያልሆነ” ማለቱ ወንጌልም ሆነ ወንጌላዊነት መሠረቱ መለኮታዊ ስጦታና ጥሪ ነው እንጂ የሰው አሳብ አለመሆኑን ያስረዳል:: በአንጾኪያ ባለችው ቤተክርስቲያን የነበሩት ነቢያትና መምህራን በጾምና በጸሎት እየተጉ እግዚአብሔርን ሲያመልኩ በነበሩበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ በርናባስንና ሳውልን ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ ማለቱ የጳውሎስ አገልግሎት ሥምሪት ሁልጊዜ በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን ሥር እንደ ነበረ የሚያስረዳ ነው:: ሐዋ 13፥1-3::
የጳውሎስ ጥሪ የተላለፈው በክርስቶስ ነበር:: በዚህኛው ምዕራፍ ላይ ደግሞ “ለጠራኋቸው ሥራ ለዩልኝ” በማለት መንፈስ ቅዱስ ሲናገር ይታያል:: ኢየሱስ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ በሥልጣንም ይሁን በፈቃድ አንድ ናቸው:: በመንፈስ ቅዱስ የተጠራ በኢየሱስ ክርስቶስ የተጠራ ነው:: በኢየሱስ ክርስቶስም የተጠራ እንዲሁ ነው:: በሌላ ቦታ ላይ የእግዚአብሔርን ለመንፈስ ቅዱስ የመንፈስ ቅዱስን ለእግዚአብሔር የሚሰጥ አገላለጽ እናነባለን:: “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” ሐዋ 20፥28:: እዚህ ላይ በገዛ ደሙ የዋጃት የሚለው ወልድን (ኢየሱስ ክርስቶስን) የሚያመለክት ሲሆን እግዚአብሔር አብ እና መንፈስ ቅዱስ በቀጥታ ተገልጸዋል:: እንዲሁም በ1ቆሮ 12፥28 ደግሞ “እግዚአብሔርም በቤተክርስቲያን አንዳንዶቹን አስቀድሞ ሐዋርያትን ሁለተኛም ነቢያትን ሦስተኛም አስተማሪዎችን . . . አድርጓል” ለሐዋርያት እውነቱን የመግለጽ ጸጋን ለነቢያትም ሐብተ ትንቢትን የሚሰጥ መንፈስ ቅዱስ ነው:: የጸጋ ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፡፡ 1ኛቆሮ 12፥4
እንግዲህ እግዚአብሔር በአካልና በግብር በስም ሦስት ሲሆን በመለኮት፣በፈቃድ፣በሕልውናና በመሳሰሉት አንድ ነው፡፡ በመሆኑም በማንኛውም መለኮታዊ አሰራር ውስጥ ሥራውን የሚሠራው ባለድርሻ ከሦስቱ አካል አንዱ ሊሆን ይችላል ሥራውን በተመለከተ የሚኖራቸው ፈቃድ ግን አንድ ነው፡፡ ሐዋርያው በገላትያ ቤተክርስቲያን ገብተው የሚያውኩትን ሐሰተኞች አፋቸውን ለማስያዝ የእርሱ ጥሪ በኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ባስነሣው በእግዚአብሔር አብ መሆኑን ገና በመልዕክቱ መግቢያ ላይ ያውጃል፡፡ “በ” የሚለው መስተዋድድ ለሁለተቱም ስሞች መቀጸሉ ኢየሱስ ክርስቶስና እግዚአብሔር አብ መካከል ያለውን የሥልጣን የፈቃድና የባሕርይ አንድነት ያመለክታል፡፡ የሁለቱን ማለትም የኢየሱስ ክርስቶስንና የእግዚአብሔር አብን የግብር ልዩነት ለማሳየት የሁለቱንም ስም ጠቅሷል፡፡
ይቀጥላል
ጸጋ ይብዛላችሁ
ኡኡኡኡኡኡኡኡ ኧራ ፀጋ ይብዘልህ iappreciate you god bless you
ReplyDeleteእግዚአብሔር ፀጋውን ያብዛለህ፡፡ Go ahead.
ReplyDeleteእግዚአብሔር ፀጋውን ያብዛለህ፡፡ Go ahead.
ReplyDeleteእግዝያብሔር ይባርክህ በበለጠ እንጠብቅሀለን በተከታታይ ትምርት
ReplyDelete