ጸሎት
የማትመረመር ሁሉን የምትመረምር፤ የማትታይ ሁሉ በፊትህ የተገለጠና የተራቆተ፤ ሐሳባችንን የምታነብ በልባችን የሚመላለሰውን ምኞት የምትሰማ እግዚአብሔር ሆይ አባታችን ነህና ተመስገን:: ጌታችን ሆነህ የመገዛት ጸጋን ሰጥተኸናልና ተመስገን:: አምላካችን ሆነህ የአምልኮ መንፈስን ሰጥተኸናልና ተመስገን:: የጠፋውን ፈልገህ የምታመጣ ከበረትህም የምታስገባ የወደቀውን የምታነሣ የደከመውን በቃልህ ጉልበት የምታበረታና ለክብርህም የምታቆም አንተ ነህና ተመስገን::
የምንታመንለትን እውነት የምንጓዝበትን መንገድ የምንኖርበትን ሕይወት አንድ ልጅህን ጌታ ኢየሱስን ስለሰጠኸን ደግሞም አንተንና እርሱን በንጹሕ ዕምነት ማወቅንም የዘላለም ሕይወት ስላደረግህልን ተመስገን:: አንተን በማመን እንድንጸና በቃልህ በኩል መጽናናት እንዲሆንልን የፍቅርህ መልዕክት የሆነውን ቅዱስ መጽሐፍ ስለሰጠኸን ተመስገን::
ጌታ ሆይ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ያለውን እውነት በማስተዋል እንድንረዳ ዐይነ ልቡናችንን ታበራ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን:: አሜን!!
መቅድመ ነገር
መጽሐፍ ቅዱስ ለምን ይጠናል?
የሰው ልጅ ባለአእምሮ ፍጥረት ነው:: ገና ጠባብና ምቹ ከሆነው ከእናቱ ማኅጸን ሰፊና አስቸጋሪ ወደሆነው ወደ ገሃዱ ዓለም ሲመጣ ማየት የሚችል ዐይን መስማት የሚችል ጆሮ መዳሰስ የሚችል እጅ እንዲሁም አጠቃላይ ሰውነት መቅመስና ጣዕምን መለየት የሚችልበት ምላስ ማሽተትና መዓዛን መለየት የሚችልበት አፍንጫ ይዞ ነው የሚወለደው::
ይሁን እንጂ ከዚህ በላይ ለጠቀስኳቸውና በቁጥር ለመወሰን አስቸጋሪ ለሆኑት ስሜቶቹ ሁሉ ዋናውንና አስፈላጊውን እገዛ የሚሰጠው የሰውነቱ /የብልቶቹ ሁሉ/ ዋናው መሥሪያ ቤት (አዛዥ ባለስልጣን) አእምሮው ነው:: እንዲያውም በሰው ልጅ የአወላለድ ሂደት በመጀመሪያ የገሃዱን ዓለም የሚቀላቀለው ጭንቅላቱ /ራሱ/ ነው:: ጠንካራ በሆነውና ከአጥንት በተገነባው ደግሞ የአጥንቱ ስፌት በሚያምረው የራስ ቅል ውስጥ ያለውን የሰው ልጅ ሁሉን ነገር የሚያውቅበትን የሚረዳበትን የሚገነዘብበትን ዋናውን የሰውነቱን ክፍል ይዞ ይወለዳል:: ዐይን፣ ጆሮና ሌሎችም የስሜት ሕዋሳት አጠቃላይ መረጃን በመሰብሰብ ለአእምሮ ያቀብላሉ:: አእምሮ ደግሞ የተቀበለውን መረጃ በየዐይነቱ በመለየት ያደራጃል፤ ያገናዝባል፤ ያብሰለስላል፤ ያንሰላስላል። በመቀጠልም አስፈላጊ የሆነውን ትርጉም በመስጠት ዕውቀት ያደርገዋል።
እንግዲህ ቁሳዊ በሆነው በዚህ ዓለም የሚኖረው የሰው ልጅ ሥጋዊ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ የሆኑትን እንዲሁም ተፈጥሮአዊ ጉዳዮችን ሁሉ ማጥናቱ የተለመደ ነው። ምክንያቱም ለማወቅ መፈለግና ማወቅ ተፈጥሮአዊ ስጦታው ነውና። ስለሆነም ሰው ይልቁንም ክርስቲያን ሊያጠናቸው ከሚገቡት ነገሮች ውስጥ ቅድሚያ መስጠት ያለበት ለመጽሐፍ ቅዱስ ነው። ጥናት ከሚጠናው ነገር ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸውን መረጃዎች በማሰባሰብና በማመሳከር ስለሚጠናው ነገር ጥልቅ ጭብጥ ወይም ጥቅል እውነት ላይ መድረስ ነው። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስ ከሚጠናበት ምክንያቶች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።
1. እምነትን ለማጠንከር
እምነት የማናየውንና ተስፋ የምናደርገውን ነገር የሚያረጋግጥ ከሰው ልጅ የአማኝነት ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ ውስጥ የሚፈልቅና የሚያድግ መንፈሳዊ ኃይል ነው። የሚያድግ ብቻም ሳይሆን የሚያሳድግም ነው፡፡“እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደተቀበላችሁት (እንዳመናችሁት)በእርሱ ተመላለሱ ሥር ሰዳችሁም በእርሱ ታነጹ” በተባለውም መሠረት ክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለኃጢአታችንም ተላልፎ የተሰጠ ቤዛችን መሆኑን በማመን መንፈሳዊ ቤት ለመሆን የምንታነጽበት ነው። ቈላ 2፥6። እንዲሁም በዚህ በዘመን መጨረሻ ላይ የምንገኝ ክርስቲያኖች የእምነታችንን ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን የምናይበት (የምንመለከትበት)ዐይናችንም ነው። ዕብ 12፥2። ደግሞም ድኅነትን ያገኘንበትን ጸጋ የተቀበልንበት ነው። ኤፌ 2፥8። ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌሉ የእረኛችንን ድምጽ ከጠላት ድምጽ ለይተን የምናውቅበት መሆኑን “በጎቹ ድምጹን ያውቃሉና ይከተሉታል” በማለት ይገልጻል። ድምጹን ማወቅ መስቀላችንን ተሸክመን እንድንከተለው ያስችለናል። ዮሐ 10፥4። የእረኛችን ድምጽ በቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ተጽፎ የተቀመጠልን መጽሐፍ ቅዱስ ስለሆነ ቃሉን ማወቅ እምነትን ማሳደግና እንዲያብብ ማድረግ ከዚያም የመንፈስ ፍሬ እንዲያፈራ ያስችላል፡፡
እንደየአማኙ ሁኔታ ታናሽ፣ ጎዶሎ፣ የሚያድግ፣ ታላቅ እምነት ሊኖረን ይችላል። ታናሹም ወደ ታላቅነት፤ ጎዶሎውም በክርስቶስ ወደሚገኝ ሙላት ፤ የሚያድገውም የወይን ግንድ በሆነው በክርስቶስ ሆኖ ፍሬ ማፍራት ታላቁም ከነውርና ከነቀፋ ርቆ ንጽሕናን ጠብቆ በቅድስና እየተመላለሰ እግዚአብሔርን በመምሰል መኖር የሚችለው ቃሉን በእምነት ሆኖ በማጥናት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ” ያለው እምነታችን በእውነትና በመንፈስ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያቆመን እንዲሆን በቃሉ መጠንከር ስላለበት ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ በውስጣችን ካለው ከእግዚአብሔር ቃል የተነሳ ፈቃዳችን ሁሉ ለእርሱ የተሰጠ ይሆናል፡፡ ቈላ 3፥16። “ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ” ተብሎ የተነገረላቸው የቤርያ ሰዎች የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት ሰምተው ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ለማመሳከር ወደ ምርምር የገቡት መጻሕፍትን ማጥናት በእምነታቸው ላይ የሚጨምረውን ጥንካሬና ዕድገት በማስተዋል ነው። ሐዋ 17፥11። በእግዚአብሔር ቃል እምነቱ የጠነከረለት አማኝ ደግሞ
· ያመነውን ያውቃል 2ጢሞ 1፥12
· በወንጌል አያፍርም ሮሜ 1፥16
· እግዚአብሔርን ብቻ ይሰማል ሐዋ 4፥19
· ወደ ግራም ወደ ቀኝም አይልም ኢያ 1፥7
· ስለ ኃጢአቱ ያለቅሳል ማቴ 26፥75 እነዚህና የመሳሰሉት ጥቅሞች ስለሚኖሩት መጻሕፍትን በማጥናት እምነትን ማጠንከር አግባብ ነው።
2. ለመታዘዝ
መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ለቃሉ በመታዘዝና ባለመታዘዝ የሚኖረውን የአቋምና የሕይወት ልዩነት እንረዳለን። ለቃሉ መታዘዝ የጽድቅ ባርያ /አገልጋይ/ ሲያደርግ አለመታዘዝ ደግሞ የኃጢአት ባርያ ያደርጋል። ስለዚህ ቃሉን ማጥናት ለተረዱት እውነት ለመታዘዝ መሆን አለበት። ይህን መድረሻ ግቡ አድርጎ የሚያጠና ሰው የጥናቱ መሠረት እምነት ስለሚሆን ላወቀው እውነት መታዘዝ አይከብደውም። የእግዚአብሔር ቃል ባጠናነው ቁጥር እምነታችንን እንደሚያጠናክር ሁሉ አመለካከታችንን ያስተካክላል፤ ግንዛቤያችንን ያሰፋል፤ ጠንካራውንም ልባችንን ይሰብራል። እንድንኖረውም ያስችለናል። መታዘዝ በተረዱት እውነት መኖር ማለት ነውና። በጌታ ዘመንም ይሁን በሐዋርያት ዘመን ለወንጌሉ አገልግሎት እንቅፋት ሆነው የነበሩት የአይሁድ ካህናት የእግዚአብሔር ቃል እየሰፋ ሲሄድ እነርሱም እውነቱን ሲረዱ ብዙዎቹ ለእግዚአብሔር ቃል ታዝዘዋል። ሐዋ 6፥7። ጌታም በወንጌሉ ምሳሌ መስሎ ሲያስተምር ለቃሉ የሚታዘዘውን ልባም ሰው ሲለው ለቃሉ የማይታዘዘውን ደግሞ ሰነፍ ሰው በማለት ገልጾታል። ማቴ 7፥24። ቅዱስ ያዕቆብም ለተበተኑት ክርስቲያኖች በጻፈው መልዕክቱ ”ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ“ ብሏል ያዕ 1፥22።
መታዘዝ በሥጋዊም ሕይወት ይሁን በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ያለው ጠቀሜታ በቃል ተዘርዝሮ በጽሑፍ ተተንትኖ የሚያልቅ አይደለም። አንድ የሥነ ሕንጻ ባለሙያ ለተማረውና ላጠናው ትምህርት ታዛዥ ሲሆን እጅግ በጣም ጥሩ ሙያተኛ ይሆናል። በጊዜ ሂደትም ትምህርቱን በተግባር ሲያዳብረው ደግሞ በጣም ተፈላጊና በሥራው ስኬታማ ይሆናል። አንድ መጽሐፍ ቅዱስ አጥኚ የሚያጠናው ለተረዳው እውነት ለመታዘዝ ከሆነም በቃሉ አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረው ኅብረት እየጠነከረ ዘወትር የእግዚአብሔር ፈቃድና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር በመሥራት ይተጋል። መታዘዝ በድርጊት ይገለጣልና።
3. ለሌላው ለመትረፍ
ሰው ማኅበራዊ ፍጥረት ነው። ክርስቲያን ደግሞ የመንፈሳዊ ማኅበር አካል ነው። እንደ ሰውነቱ የሚኖረውም ከሰው ጋር ስለሆነ ያወቀውን የማሳወቅ ያየውን የመመስከር ኃላፊነት አለበት። ምስክርነቱ የበረታ እንዲሆንና ተደማጭነትን እንዲያገኝ ግን ቃሉን ያጠና መሆኑ አስፈላጊ ነው።ጌታ ደቀመዛሙርቱን ለሦስት ዓመታት ያህል ከእርሱ ጋር እንዲቆዩ ያደረጋቸው ቃሉን በአግባቡ እንዲማሩና እንዲያጠኑ ከዚያም ለሌላው መትረፍ እንዲችሉ ነው። ማቴ 4፥18፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ የሰሙትን ስለማሰማት ሲናገር “ባልሰሙትስ እንዴት ያምናሉ? ያለሰባኪስ እንዴት ይሰማሉ? በማለት ይጠይቅና “እምነት ከመስማት እንደሆነ መስማትም የእግዚአብሔርን ቃል መሆኑን ያረጋግጣል። የሚያሰማውም ሰባኪ/የተረዳውን ለማስረዳት የተዘጋጀ ሰው/ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ሮሜ 10፥14-17፡፡ ስለዚህ ወዳጄ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚያስፈልግህ ወገንህን ከጥፋት ወደ ድኅነት ከሞት ወደ ሕይወት መመለስ እንድትችል ነው። አንዳንዶችንም ከጥፋት ነጥቃችሁ አድኑ እንደተባለ በጥፋት ውስጥ ላሉት ደራሽ እንድትሆን ያስችልሃል። መጽሐፍ “የልብ መዘጋጀት ከሰው ነው” በሚለው መሠረት ለሚጠይቁ ሁሉ መልስ ለመስጠት በሚያስችል መጠን ያጠና ሰው ለሌላው መትረፍ ይችላል፡፡
4. ዘወትር ከእግዚአብሔር ጋር መሆንን ለማረጋገጥ
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ራሱን ከገለጠባቸው መንገዶች አንዱ ቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ በሚገኘው ቅዱስ ቃሉ ነው። በቅዱስ ቃሉ ውስጥ እግዚአብሔር ከሰው ጋር ያለውን ግንኙነት ሲገልጽ:-
· ሰውን በመልኩና በምሳሌው እንደፈጠረ ዘፍ 1፥26
· ለሚፈልጉት ሁሉ መገኘት እንደሚችል ኤር 29፥13
· የቅርብ አምላክ መሆኑን ኤር 23፥23
· እርሱን የሚያምኑ የሚሣናቸው እንደሌለ ማቴ 17፥20 ፣ፊል 4፥13
· እርሱን የሚያምኑ ባሉበት እርሱም በዚያ እንደሚሆን ማቴ 18፥20፣28፥19
· ከሁሉም በላይ ልዩ ስጦታን/ አንድያ ልጁን/ በመስጠት ለሰው ያለውን ፍቅር ማስታወቁንና ሌሎችንም ዮሐ 3፥16 ።
ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ስለተፈጠረ የእግዚአብሔር የሆነ ነገር ብቻ አእምሮውን ይገዛዋል ልቡንም ያረካዋል። ስለዚህ እግዚአብሔር ትውልዳችንን የሚናገረው በቃሉ አማካኝነት ስለሆነ መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ለሕይወታችን የሚረባንን መለኮታዊ አሳብ በማግኘት ከእግዚአብሔር ጋር መሆናችንን ማረጋገጥ እንችላለን ። ብዙ ጊዜ አስተውላችሁ ከሆነ የሰውን ስም አንስታችሁና ስለ እርሱ አውርታችሁ ሳትጨርሱ ያ ሰው ሊመጣ ወይም ስልክ ሊደውል የሚችልባቸው አጋጣሚዎች ይበዛሉ። በዚህ ጊዜ ታዲያ ያ ሰው ከመጣ ወይም ከደወለ ንግግራችሁ የሚጀምረው ዕድሜህ ረጅም ነው። አሁን ስናነሣህ ነበር በሚል ይሆናል። ስለዚህ አሳባችንን ያተኮርንበት ነገር ወደ እኛ እንዲሳብ የሚያደርግ ተፈጥሮአዊ የሆነ የስበት ሕግ አለ ማለት ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም እኔው ራሴ ብዙ ገጠመኞች አሉኝ። በአብዛኛው በልቤ ያሰብኳቸው ሰዎች ይደውላሉ። ወይም ይመጣሉ። በዚያ ጊዜ እጅግ ይገርመኛል። የሥነ ልቡና ሊቃውንት ይህንን ”ቴሌፓዚ“ በሚል ይገልጡታል። ሰው ከሰው ጋር የሚኖረው ግንኙነት መሠረት የሚያደርገው አስተሳሰቡ ላይ ከሆነ በእምነት ሆነን መጻሕፍትን ለማጥናት አሳባችንን ስንሰበስብና በምናጠናው መጽሐፍ ክፍል ላይ ስናተኩር ደግሞ ከአምላካችን ጋር መቀራረብ እንደምንችል መረዳት አያዳግትም። በመጽሐፍም የኤማሁስ መንገደኞች ጌታ ኢየሱስን ያገኙት በጉዟቸው ስለ እርሱ በመጨዋወታቸው ነው።
5. ራስን ለማወቅ
ሰው ጠያቂ አእምሮ ያለው ፍጥረት እንደመሆኑ በተማረውም ባልተማረውም ሰው አእምሮ የሚፈጠሩና የሚመላለሱ ብዙ ጥያቄዎች ይኖራሉ። ለሁሉም ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ማግኘት የሚቻለው ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። ለምሳሌ ሕይወት ምንድን ናት? ዓላማዋስ ምንድን ነው? ከየት መጣች? ወደ የት ትሄዳለች? ሰው በዚህ ምድር ሲኖር ምን ማድረግ አለበት? ከሞት በኋላ ሕይወት አለ? እነዚህና የመሳሰሉት ፍልስፍናዊ ይዘት ያላቸው ነገር ግን ያመነ ሰው ብቻ መጻሕፍት ውስጥ ሲገባ ተገቢውን ምላሽ የሚያገኝላቸው ጥያቄዎች ናቸው።ሰው ከራሱ ውጭ ስላለው ነገር ከማወቁና ከመረዳቱ በፊት መጀመሪያ ማወቅና መረዳት ያለበት ራሱንና ስለራሱ ነው። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ ራሳችንን ለራሳችን ሲያስረዳን ሰው:-
· ሕያው ነፍስ ያለው ፍጥረት እንደሆነ ዘፍ 2፥7
· ኑሮው በጥረት የተመላና ሟች መሆኑ ዘፍ 3፥17
· ትውልድን የመተካትና የመንከባከብ ኃላፊነት እንዳለበት ዘፍ 1፥28፣ ኤፌ 6፥4
· በፍጥረት ላይ ባለሥልጣን እንደሆነ ዘፍ 1፥26
· ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ባሕርያዊ ትስስር ዘፍ 1፥26፣ ዕብ2፥16፣2ጴጥ 1፥3
· ለእግዚአብሔር ብቸኛው ተወዳጅና ተፈቃሪ መሆኑን 1ኛ ዮሐ 4፥7-11
· ከጊዜያዊ ሕይወት ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ሞት በተባለው መሳፈሪያ /መጓጓዣ/ ተጭኖ ከዚህ ዓለም እንደሚሄድ
· በዘላለም መንግሥት ውስጥ የንጉሡ የእግዚአብሔር ሠራዊት ሆኖ እንደሚኖርና ሌሎችንም እውነታዎች ይገልጽልናል
6. ስለ እግዚአብሔርና እግዚአብሔርን ለማወቅ
እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነው። ማወቅ የሚችል ፍጥረትን የሰውን ልጅ የፈጠረ ፈጣሪ ነው። እግዚአብሔር የሚታየውም ይሁን የማይታየው የገዘፈውም ይሁን የረቀቀው ፍጥረት ፈጣሪ ነው። ከባሕርይው ስፋትና ጥልቀት የተነሣ ሊመረመር አይቻልም። ከጥበቡም ርቀት የተነሣ ፈጥሮ ማናገር የሚችል ጌታ ነው። ስለሆነም በፈጠረው ፍጥረት ይልቁንም በሰው ልጅ ዘንድ መታወቅ ይፈልጋል። ስለ እግዚአብሔር ማወቅ ሲባል ማንነቱን፣ ባሕርይውን፣ ሥራውንና አኗኗሩን አእምሮ ሊረዳ በሚችል መጠን መገንዘብ /መረዳት/ ማለት ነው። ይህ የፍጥረት ሁሉ የጋራ እውቀት /መረዳት/ ነው። እግዚአብሔር ፈጥሮ ማናገር የሚችል ከመሆኑ የተነሣ እርሱ እንዲመሰክሩ ከፈቀደ ስለፈጣሪው የማያውቅና የማይናገር ፍጥረት አይኖርም። ሰው ስለ እግዚአብሔር የሚያውቅበት መንገድ ግን እምነትን መሠረት ያደረገ ስለሚሆን ከላይ የጠቀስናቸውን ማለትም የእግዚአብሔርን ማንነት፣ ባሕርይ፣ አኗኗርና ሥራ ከሌላው ፍጥረት በተለየ መልኩ መገንዘብ ይችላል።
ይሁን እንጂ ስለ እግዚአብሔር ማወቅ እና እግዚአብሔርን ማወቅ ግን የተለያዩ ነገሮች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ታሪክ መጽሐፍ እንደመሆኑ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያለውን እውነተኛ ትረካ ጠንቅቆ መረዳትን ሲጠይቅ፤ ሁለተኛው ግን በቃሉ መሠረት የተተረከውን እግዚአብሔርን በሕይወት ማወቅን ይጠይቃል። ስለ እግዚአብሔር በመማር፣ በማንበብና ፍጥረትን በማየት ማወቅ ይቻላል። እግዚአብሔርን ግን በሕይወት በመኖር ብቻ ነው ማወቅ የሚቻለው። በመጽሐፍም ”እውነተኛ አምላክ ብቻ የሆንህን አንተን የላክኸውንም ኢየሱስ ክርስቶስን ያውቁ ዘንድ ይህች የዘላለም ሕይወት ናት“ ይላል ዮሐ 17፥3። እንዲሁም ”እግዚአብሔርን ፈልጉ በሕይወት ትኖረላችሁ“ በማለት ነቢዩ አሞጽ በሕይወት ለመኖር እግዚአብሔርን መፈለግ /በሕይወት እግዚአብሔርን ማወቅ/ ግድ መሆኑን ሲያስረዳ ነቢዩ ሆሴዕ ደግሞ እግዚአብሔርን በሕይወት /በኑሮ/ አለማወቅ ከፍተኛ ጥፋት መሆኑን ”ሕዝቤ ዕውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል“ ተብሏል ሆሴ 4፥6።
7. ስለ ሁሉም ነገር የሚናገር መጽሐፍ ነው
መጽሐፍ ቅዱስን ከሌሎች መጻሕፍት ልዩ የሚያደርገው ስለ ሁሉም ነገር መናገር የሚችል መጽሐፍ መሆኑ ነው። በዓለማችን ብዙ ጠበብት የጻፏቸው ብዙ ደራሲያን የደረሷቸው መጻሕፍት አሉ። እነዚህ መጻሕፍት አንድ ትውልድ በዘመኑ የነበረውን የአስተሳሰብ አቅጣጫ የአመለካከት ስፋትንና የግንዛቤ ብስለት ያመለክታሉ። ሆኖም አንድ መጽሐፍ ሊናገር የሚችለው ስለ አንድ ጉዳይ ነው። በዓለማችን ያሉት ጉዳዮች ብዙ ከመሆናቸው የተነሣ እጅግ በጣም የብዙ ብዙ መጻሕፍት ቢጻፉም እንኳ ጉዳዮቹ ግን ገና አልተነኩም። አሁንም የሚጻፍበት ጉዳይ ለድርሰት የሚሆን አሳብ አለ።
ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ስንመለስ ደግሞ በአንድ ጥራዝ ውስጥ የተሰበሰቡትን መጻሕፍት ጥቂት ቢሆኑም በውስጣቸው ያለው ፍሬ አሳብ ግን ሁሉንም ጉዳዮቻችንን የሚዳስስ ነው። ይህም ማለት ከፍጥረት ጅማሬ እስከ ዓለማችን ፍጻሜ የሆነውንና እየሆነ ያለውን እንዲሁም የሚሆነውን ነገር ሁሉ በራሱ የጊዜ ቀመርና ስሌት እንዲሁም ያለ ምንም አድልዎና ወገናዊነት ይገልጻል። ስለዚህም የማኅበራዊ ሳይንስ፣ የጤና ሳይንስ፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ የታሪክ ተመራማሪዎች እንዲሁም የሥነ ሕንፃና ሌሎች የጥናት መስኮች ሁሉ መነሻቸው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ከዚህም በላይ ስላለፈው ነገር የሚናገር መጽሐፍ በመሆኑ የማያረጅ የአሁኑንም ዘመን ሁኔታ በመናገሩ ዘመናዊ የማይባል ስለሚመጣው የሚናገር መጽሐፍ በመሆኑም ትንቢታዊ ብቻ ያልሆነ ለትውልድ ሁሉ የሚስማማ ብቸኛ መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
ስለከበሩት ሰዎች ክብር እንደሚናገር ሁሉ ስለወደቁትም በዚያው መጠን ይናገራል። ስላመኑት እንደሚናገር ሁሉ ስለካዱትም ይናገራል ጻድቁ ጽድቁን ቢተውና ኃጢአተኛ ቢሆን የቀደመውን ጽድቅ እያሰበም ኃጢአቱን ግን ይዘረዝራል። ስለዚህ በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ የሚገጥመውን ሥጋዊና መንፈሳዊ ውጣ ውረድ ሰው ከእግዚአብሔር ጋር እግዚአብሔርም ከሰው ጋር እንዲሁም እግዚአብሔርም ሆነ ሰው ከሌሎች ፍጥረታት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ይዘረዝራልና መጠናት ይገባዋል።
8. የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ
በዓለማችን የሚገኙ ብዙ ዓይነት መጻሕፍት የመጻፋቸው ምክንያት የጽሐፊያኑ ዕውቀት ዝንባሌ የሕይወት ልምምድና ስለጻፉት ነገር ያላቸው ምልከታ ሊሆን ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን የመጻፉ ምክንያት የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ ብቻ ነው። የሰው ልጅ ጤናማ የሆነ ተፈጥሮአዊ የመዘንጋት ስጦታ ስላለው ዘወትር ከአጠገቡ ሆኖ የሚያስታውሰው የሚመራው የሚያስተምረውና የሚመክረው ጠባቂ ያስፈልገው ነበር፡፡ ከረቂቃኑ መላዕክት ይልቅ በወረቀት ላይ የሰረፈው የእግዚአብሔር ቃል ቢሆን እንደሚሻል እግዚአብሔር ስላወቀ የአባትነቱን ደብዳቤ መጻሕፍትን ሰጠ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እንኳ የእግዚአብሔር ቃል ቢሆንም እንዲሁ ከሰማይ መውረድ ስላልነበረበት የሚጽፉትን የሚያደራጁትን ሰዎች እግዚአብሔር ራሱ መረጠ፡፡ ጸሐፊያኑም ሲመረጡ መለኪያቸው የኑሯቸው ሁኔታ፣ የትምህርታቸው ደረጃና የሥነ ጽሑፍ ልምዳቸውን በማወዳደር አልነበረም፡፡ ለእኛ በማይታዩ ለእርሱ ብቻ በተገለጡ መስፈርቶች ጸሐፊያኑን መረጠ፡፡ የሚመራቸውን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ ሰጣቸው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ተጻፈ፡፡
ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል እንደመሆኑ ዘመናትን የሚሻገር ለትውልድ ሁሉ የሚስማማና ለሰው ልጅ ሥጋዊና መንፈሳዊ አካሄድ መመሪያ ለመስጠት እንዲሁም እያንዳንዱን ለመዳኘት ለመምከርም ሆነ ለመገሰጽ ብሎም ለማስተማር አቅም ያለው ባለስልጣን መጽሐፍ ነው፡፡ ስለዚህ እግዚአብሔር በቃሉ በኩል ለየጉዳዮቻችን የሚኖረውን ፈቃድ ለመረዳት መጽሐፍ ቅዱስ ይጠናል
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ :
· መዳን ይገኝበታል ፣ጥበብን ይሰጣል 2ጢሞ 3፥15-17
· በምስክርነቱ አንድ ወጥ ነው ሉቃ 24፥27፤ 44
· በትንቢትነቱ ትክክል ነው 1ጴጥ 1፥10-12
· ተፈጻሚነት ያለው ነው ዮሐ 19፥24፣ 28፣ 36፣ 37
· የሚሠራ ነው 1ተሰ 2፥13 ፤ ዕብ 4፥12
· ዘላለማዊ ነው መዝ 118፥89
· የሚቆጣጠር ባለሥልጣን ነው መዝ 118፥11
· የማይገደብ መገለጥ አለው ዕብ 1፥1-3
· መለኮታዊ ነው 2ጴጥ 1፥19
· የቃሉ ተስፋ የሚታመን ነው 2ቆሮ 1፥20
· ሕያው ነው 1ጴጥ 1፥23
· ሲማሩት ያሳምናል ሮሜ 10፥17
· የሚያድግ የሚሰፋና የሚያሸንፍ ነው ሐዋ 19፥19 ፤ 6፥7
· እርግጠኛ ነው ዮሐ 5፥24፤ 20፥31
· ክርስቶስን ይገልጣል ዮሐ 5፥39
· እግዚአብሔር ስለሁለንተናችን ያለው ዕውቀት ተገልጾበታል መዝ 138፥1
መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት ይጠናል?
መጽሐፍ ቅዱስ ሲጠና የሚከተሉት ነጥቦች መሠረታዊ ግብዓቶች ከሆኑ ጥናቱ ውጤታማ ይሆናል::
1. በጸሎት
ጸሎት ለማንኛውም ሥራ መጀመሪያ ነው:: ሥራውና ለሥራው የሚኖረንን ተነሣሽነት ሥራውን የመሥሪያ ጊዜና ጥበብ ለሰጠን አምላክ ምስጋና እናቀርባለን:: በመቀጠልም በሥራው ሂደት ውስጥ የጀመርነውን የሚያስፈጽመንን ጸጋ እንዲያበዛልን በጀመርንበት ተነሣሽነት እንድንፈጽመውም ትጋትን እንዲያጸናልን እንለምንና በሥራችን ፍጻሜ ለማመስገን እንዲያበቃን ለምነን ሥራችን ይጀመራል:: በሥራችንም ፍጻሜ የጅማሬ፣ የሂደትና የፍጻሜ ባለቤት የሆነውን ንጉሥ አመስግነን የጊዜው ሥራችን ይጠቃለላል::
ይሁን እንጂ ጸሎት የትልቅ ሥራ መጀመሪያ ወይም ስለትልቅ ሥራ መጸለይ ብቻ ሳይሆን ንጹሕ ቅዱስ ከሆነውና ሁሉ ነገራችን በፊቱ ተገልጦ ከሚታይለት ጌታ ጋር የሚኖረን ቆይታ እንደመሆኑ መጠን ጸሎት በራሱ ትልቅ ሥራ ነው::
መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፈ መጽሐፍ ስለሆነ ሊጠና የሚችለውም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት ነው:: የመጽሐፍ ቅዱስ ቅድስና መሠረት የሚያደርገው የባለቤቱን የእግዚአብሔርን ቅድስና ነው እንጂ የጸሐፊያኑን ቅድስና አይደለም:: ይህ ማለት ጸሐፊያኑ ቅድስና ሊኖራቸው አይገባም ማለት አይደለም:: በመሆኑም በዚህ የቅድስና መጽሐፍ ውስጥ ያለውን መለኮታዊ አሳብ ለመረዳት /ለማጥናት/ በጸሎት መንፈስ መሆን ያስፈልጋል::
2. የጥናት መርሐ ግብር ማዘጋጀት
መጽሐፍ “ለሁሉም ጊዜ አለው” እንደሚለው ሁሉ በቀን ውስጥ ለእያንዳንዳችን በእኩልነት ያለንን 24 ሰዓት በመከፋፈልና ለሥራዎቻችን እንደ አስፈላጊነቱ ቅደም ተከተል ስንሰጥ አንዱን ጊዜ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማዋል:: ሰውነታችን በቀን ውስጥ የሚያስፈልገውን የምግብ አቅርቦት እንደየኑሮአችን ሁኔታ እንሰጠዋለን:: መንፈሳዊነትም በራሱ ሕይወት ስለሆነ ምግብ ያስፈልገዋል:: ስለዚህ ነበር ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በኦሪት የተነገረውን ቃል ለማጽናት በወንጌል “ሰው ከእግዚአብሔር አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በእንጀራ ብቻ አይኖርም” በማለት የተናገረው:: ማቴ 4፥4:: በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን የምናጠናበት መርሐግብር ካለን ከምናጠናው የእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ለሕይወታችን የሚሆን የአምላካችንን ፈቃድ በየዕለቱ እንቀበላለን:: የመንፈሳዊ ሕይወታችንም ምግብ ነውና እናድግበታለን::
ሥራዎችን በመርሐ ግብር /በቅደም ተከተል/ መሥራት ያስተማረን እግዚአብሔር ነው:: በፍጥረት ሥራው ውስጥ ፍጥረትን የሠራበትን ቅደም ተከተል ብንመለከት በመርሐ ግብር ውስጥ ያለውን ውበት ማስተዋል እንችላለን:: ሰማይንና ምድር በመዘርጋት የተጀመረው ሥራ የፍጥረት ጉልላት የሆነውን ሰውን በመፍጠር ሲጠቃለል ዕጹብ የእርሱ ሥራ ያሰኛል:: ስለዚህ ዕለታዊ፣ ሳምንታዊ፣ ወርኃዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ዕቅድ በማዘጋጀት ማጥናት ይቻላል:: በመርሐ ግብር መመራት በውስጣችን ያለውና የተሰራንበት የእግዚአብሔር ባሕርይ መገለጫ ነው::
3. በጽሞና ማንበብን መለማመድ
አካል ባለበት ቦታ ላይ መንፈስን አሳርፎ በሚያነቡት ነገር ላይ አሳብን አነጣጥሮ /አተኩሮ/ ማንበብ ለመጽሐፍ ቅዱስ አጥኚ ተገቢ ነው:: የዐረፍተ ነገሩ አወቃቀር የቃላት አገባብና የአሳቡ ተፋሰስ ግልጽ እንዲሆን ያደርጋልና:: በዚህም ሂደት ውስጥ ጸሐፊው ያተኮረባቸውን ታሪሎች ምሳሌዎች ኃይለ ቃላትና በየአንቀጹ ውስጥ ያሉትን ፍሬ አሳቦች ለማግኘት ይጠቅማል:: አንዳንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስ ሳነብ አይገባኝም የሚለው እንዲገባው ተዘጋጅቶ ስለማያነበው ነው:: በጽሞና ለማንበብ የተዘጋጀ ሰው የሚያነብበትን ቦታ ይመርጣል /ያመቻቻል/ ካነበበው ገጸ ንባብ ውስጥ የተረዳውን ነገር በራሱ ቋንቋ /የአገላለጽ ስልት/ ይጽፋል /ማስታወሻ ይይዛል/:: እንዲሁም የንባቡን ሰዓት ወደ ማጠቃለል ሲደርስ በመጨረሻዎቹ ጥቂት ደቂቃዎች ያነበበውንና የያዘውን ማስታወሻ ማገናዘብ::
4. መተርጎም
ምንም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስን ለመረዳት የሚያገለግሉ ሌሎች አጋዥ መጻሕፍት ቢኖሩም መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን በራሱ የሚተረጉም መጽሐፍ ነው:: ሌሎች የትርጓሜ መረጃዎችን ከመጠቀም አስቀድሞ ራሱን በራሱ እንዲተረጉም በማድረግ ከተነበበው ገጸ ንባብ ውስጥ ያለውን ምስጢረ ነገር /መለኮታዊ አሳብ/ መረዳት:: ትርጓሜ እያንዳንዱ በመጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ ታሪክ እና ምሳሌ የሚያመለክተውን እውነት ትንቢቱም የሚያሳየውን ፍጻሜ አጥርቶ ለማየትና ለመገንዘብ ያግዛል::
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የኤማሁስን መንገደኞች አለማስተዋልና ልባቸው ከማመን መዘግየቱን ከነቀፈ በኋላ ስለ እርሱ በሙሴና በነቢያት የተነገረውን እየተረጎመ አስተምሯቸዋል:: ሉቃ 24፥27:: ከዚህ በተጨማሪ ሌሎች የትርጓሜ መጻሕፍትንና የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት በመጠቀም የትርጓሜን አቅጣጫ ማስፋፋት ይቻላል::
5. የጥናታችንን መሠረት እምነት በማድረግ
እምነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መሠረት ነው:: ባመነ ልብ ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የአእምሮአችንና የአስተሳሰባችን አድማስ ድረስ እንድንጓዝ ያስችለናል:: መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች በሰዎች ቋንቋ የተጻፈ መጽሐፍ ቢሆንም በውስጡ የያዘው አሳብ ግን መለኮታዊ ስለሆነ መረዳት የሚቻለው በእምነት ብቻ ነው:: መጽሐፍ ቅዱስ የእምነት መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን አማኝ መጽሐፍም ነው:: ምክንያቱም በመጀመሪያው ምዕራፍና ቁጥር የሚናገረው ስለ እግዚአብሔር ሥራ ነው እንጂ የእግዚአብሔር ሕልውና ጉዳይ ጥያቄው አልነበረምና:: በመጀመሪያ እግዚአብሔር ነበረ አይደለም የሚለው:: “በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” ነው የሚለው:: ሥራ ደግሞ የሚያሣየው የሠራተኛውን ሕልውና /መኖር/ ነው:: ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ እግዚአብሔር መኖሩን በማመን የሚጀምር መጽሐፍ ነው:: በመጀመሪያ ለአንባቢያን ማስገንዘብ የሚፈልገው ስለእግዚአብሔር ሥራ ነው እንጂ ስለእግዚአብሔር ሕልውና አይደለም:: ስለዚህ አንባቢው በእምነት ሆኖ ቢያነበው የእግዚአብሔርን አሳብ በአግባቡ እየተረዳ ማንበብ ይችላል::
ይህም ሆኖ ውስን በሆነው በሰውነት አእምሮ የማይደረሰስባቸው መለኮታዊ አሳቦች መኖራቸው የማይቀር ነው:: ዳዊት “እውቀትህ ከእኔ ይልቅ ተደነቀች፤ በረታችም ወደ እርሷም ለመድረስ አልችልም” በማለት እንደዘመረው ከመጽሐፍ የምናነበው ነገር አሁን ካለንበት ከገሃዱ ዓለም አሳብና አካሄድ ጋር የማይስማማ ነገር ግን በእምነት ከዓለም ርቀን ስንጓዝ ከፍ ያለው የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ አሳብ ወደ መረዳት ማደግ እንጀምራለን:: አሁን ከእውቀት ከፍለን እናውቃለን በኋላ ግን ሁሉን እናውቃለን ተብሏልና:: መዝ 138፥6፤ 1ቆሮ 13፥12::
6. የተረዳነውን በመተግበር /በሕይወት/
ይህን ነጥብ በተመለከተ ጥቂትም ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ለምን ይጠናል በሚለው ክፍል 6ኛ ቁጥር ላይ የተመለከትነው ቢሆንም አሁን ጥቂት አክልበታለሁ:: የክርስትና መርሆ እምነት ወደ ትምህርት፣ ትምህርት ደግሞ ወደ ድርጊት የሚል ነው:: አብርሃም እግዚአብሔር /አንድ ታላቅ ኃይል/ መኖሩን አመነ:: ያመነውን ለማወቅ ምርምር ጀመረ ዐወቀው፤ ካወቀው እግዚአብሔር ጋር ተለማምዶ (ተስማምቶ፣ ተግባብቶ) ኖረ:: መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ስላመነው አምላክ ያላወቅናቸውን ዘርፈ ብዙ ነገሮች እንድናውቅና በዚያ በደረስንበት እንድንመላለስ ያደርገናል::
በዓለማችን ከሚገኙ ከሌሎች መጻሕፍት መጽሐፍ ቅዱስ ልዩ ከሚሆንባቸው ምክንያቶች አንዱ ከተጠና በኋላ ያወቁትን በእምነት አዋህደው በተግባር ቢገልጡት በኑሮ ውስጥ እግዚአብሔርን ማሣየት እንድንችል ማድረጉ ነው:: ጌታችን በወንጌል ሲያስተምር “የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን” ብሏል:: ዮሐ 14፥23:: ሕያው አምላክ የዘላለም መኖሪያችን እንደሚሆንና የዘላለም ክንዶቹም ሳይዝሉ እንደሚሸከሙን የተነገረለት እርሱ አሁን ደግሞ በቃሉ ወደ ሚኖረው እንደሚመጣና ከእርሱ ጋርም እንደሚኖር ተነገረ:: ቅዱስ ያዕቆብም “ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ” እያለ የእግዚአብሔርን ቃል ማወቅ ወደ ድርጊት ሊመራ እንደሚችል ያስገነዝባል:: ያዕ 1፥22:: ቅዱስ ጳውሎስም ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች በጻፈው መልዕክቱ “ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ” በማለት የአንድ መጽሐፍ ቅዱስ አጥኚ ሕይወት ከቃሉ ጋር የተስማማ ከሆነ ክርስቶስን በመምሰል በቅድስና መኖር እንዳለበት ያስተምራል:: በርግጥ የእግዚአብሔር ቃል በትክክል ተሰበከ ማለት የሚቻለው ከቃል ይልቅ በተግባር ሲገልጽ ነው:: “ተገባር ከቃል ይልቅ ይናገራልና”::
ጸጋ ይብዛላችሁ !!! ይቀጥላል ……..
የመድኃኒት ንግድ ሥራዬን ለማስፋፋት በተጠቀምኩበት ብድር ለመርዳት ሚስተር ቤንጃን ከሚያስፈልጓቸው በላይ አልፈዋል ፡፡
ReplyDeleteእነሱ ለመስራት ወዳጃዊ ፣ ባለሙያ እና ፍጹም ዕንቁዎች ነበሩ ፡፡ እኔ ለማነጋገር ብድር የሚፈልግን ማንኛውንም ሰው እመክራለሁ ፡፡ Lfdsloans@outlook.com.WhatsApp ... +19893943740.