እግዚአብሔር አይችልም
በታላቅ ግርማ በማይመረመር እውቀትና በማይቆጠር ጥበብ ለአኗኗሩ መነሻ ለዘመኑ ፍጻሜ የሌለው ብቸኛው አምላክ እግዚአብሔር ነው:: ምንም እንኳ ምድራችን ራሳቸውን በሠራዊት ብዛት፣ በዘመነኛ የጦር መሣሪያና ስልት ያስታተቁ ታላላቅ ተብዬዎች የበዙባት ብትሆንም ትልቅነታቸው ከጌታችን ጋር አይነጻጸርም:: “ጌታችን ታላቅ ነው ኃይሉም ታላቅ ነውና” እንዲሁም ዓለም የሠለጠነ የሰው ኃይል ቢያከማች የረቀቀ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ቢጠቀም ኃይሉ ግን የሚመጠን፣ የሚለካና የሚገደብ እንዳይቋረጥም ከፍተኛ ጥንቃቄ በተመላበት ቁጥጥር የሚጠበቅ ነው፡፡ የጌታችን ኃይል ግን ከዚህ ይለያል:: ታላቅ ነውና፡፡”እግዚአብሔር ታላቅ ነው” አምላካችን ታላቅ የተባለው እንደ ፍጥረት ሥርዓት የሚለካበት መለኪያ ኖሮት አይደለም፡፡በጠንከራ ክንዱ ጊዜና ሥልጣን፣ሐብት፣ትዕቢትና ዕውቀት ያተለቃቸውን ሁሉ በረቂቅ ጥበቡ የሚያሳንስ እርሱ ስለሆነ ነው፡፡ የቋንቋችንም አድማስ ከዚህ ቃል ማለፍ አይችልም፡፡ ደግሞስ “አቤቱ አንተ ብቻህን ታላቅ አምላክ ነህ” አይደል የተባለው፡፡መዝ 95፥4፣85፥10
አዎ የእኛ ጌታ እጁን ዘርግቶ ይቅርና ከአንደበቱ ቃል ሳይወጣ በልቡ ፈቃድ ብቻ የገዘፈውን ሰማይና ምድር የሠራ ነው:: በየትኛውም ዘመን ትውልድ የአስተሳሰብ እድገት ሊደርስበት የማይችል ብርሃንን በይሁንታ የፈጠረ ነው፡፡ ለምድር ኪስ አበጅቶ ሰፊ ባደረገው ኪሷ ያስቀመጠውን ውሃ ውቅያኖስ ያለው በጠባቦቹ ኪሶቿ ያስቀመጠውን ውሃ ደግሞ ባሕር እያለ የጠራው እርሱ ነው :: ዘርዝረን የማንፈጽመውን ሥራዎቹን ያከናወነበትን ኃይል ደግሞ ከነቢዩ ጋር “ኃይልህ ታላቅ ነው አንተ ባሕርን በኃይልህ አጸናሃት” እንዲሁም “ኃይልህ ብዙ ነው” እንለዋለን፡፡ መዝ 65፥3 ፣73፥13
እግዚአብሔር እርሱ ሠርቶ ይቅርና ሲያሠራም ኃይሉ ታላቅ ነው:: በሙሴ በትር ላይ የተገለጠው ኃይሉ ባሕር ሲከፍል ከዓለት ላይ ውሃ ሲያፈልቅ በእምነት አይተናል:: በእስራኤል ጩኸት ውስጥ የኢያሪኮን ቅጥር /ግንብ/ ሲያፈርስ አስተውለናል:: “ለእግዚአብሔር ዘምሩ የኃይል ቃል የሆነ ቃሉን እነኾ ይሰጣል” ተብሏል መዝ 67፥33:: ደግሞስ “እንደ እግዚአብሔር ያለ ማንም የለም” የተባለው በእውነት እንደርሱ ያለ ማንም ስለሌለ ነው :: የባሕሩን ኃይል ሲገዛ ሞገዱንም ጸጥ ሲያደርገው ነፋሱንም ሲገስጽ በፈጠረው ፍጥረት ላይ ከፍተኛው ባለሥልጣን እርሱ ብቻ መሆኑን አስታውቋል:: ፍጥረት ሁሉ የኃይሉ መገለጫ የጥበቡ ማስታወቂያ ነው:: መዝ 88፥9፣ ማቴ 8፥23፤ 27::
እግዚአብሔር ለሚያምኑትና ለሚታመኑበት ሁሉ ነገሮችን የሚያከናውንበት ኃይል ከጠላት የሚከለሉበት ጋሻ መሆኑን “እግዚአብሐር ኃይሌና ጋሻዬ ነው ልቤ በእርሱ ታመነ እኔም ተረዳሁ” በሚለው ዝማሬ መገንዘብ ጠቃሚ ነው መዝ 27፥7:: የሰው ልጅ በራሱ አንዳች ኃይል ስለሌለው ከአምላኩ የተሰጠውን ተፈጥሮአዊ ኃይል ጠቃሚ በሆነ መንገድ ለማዋል በሕይወቱ ውስጥ እግዚአብሔርን ማኖር አለበት:: “ኃይሌን ወደ አንተ አስጠጋለሁ” በእኔ ውስጥ አንተ እንድትሠራ እፈቅዳለሁ ተብሏል:: እንግዲህ እግዚአብሔር በሕይወታችን የሚኖር ከሆነ ሁለንተናችን በኃይል የተመላ ማስተዋላችንም ጥበብ የበዛበት ይሆናል::
መዝሙረኛው ስለጌታችን ታላቅነት እና ስለኃይሉም ታላቅነት ተናግሮ ብቻ ዝም አይልም:: ስለጌታችን ጥበብ ስፋትና ጥልቀት እንዲሁም በሰው ቁጥር ሊቀመርና በሰው አእምሮ ሊስተዋል እንደማይችል ለማስገንዘብ “ለጥበቡም ቁጥር የለውም” ይላል መዝ 146፥5:: ዓለማችን ብዙ የጥበበኞች፣ የአዋቂዎችና ብልሃተኞች ክምችት ያሉባት ናት:: በየዘመናቱ የሚኖሩት የሥልጣኔ ሂደቶች፣ ለውጦች እና እድገቶችን ስንመለከት በእውነትም ዓለም ብዙ ጥበበኞችና አዋቂዎች ብልሃተኞችም አሏት ያሰኛል:: የሚገርመው ግን ከእነዚህ ሁሉ ጥበብና ዕውቀት የእግዚአብሔር ሞኝነት ይልቃል:: እስቲ ቅዱስ ጳውሎስ እግዚአብሔርን እንዴት እንደ ተረዳው እናስተውል? “ከሰው ይልቅ የእግዚአብሔር ሞኝነት ይጠበባል” ያለው ለምን ይሆን? የግሪክን ጥበበኞች በፍልስፍና አደባባዮቻቸው የብዙዎችን ጆሮ የያዘ ብዙ የፍልስፍና ንግግሮችን ሲያደርጉ አላያቸውም ነበር ?:: አይቷቸዋል ፡፡ ነገር ግን ዘመናቸውን በፍልስፍና ጥበባቸው የተቆጣጠሩ የግርክ ምሁራን በአምልኮ ስፍራቸው መሠዊያ ላይ “ለማይታወቅ አምላክ” የሚል ጽሑፍ አኑረው ሲመለከት ሳያውቁ የሚያመልኩትን አምላክ ሊያሳያቸው ተነሣ፡፡ከዚህ ዓለም ጥበበኞች የእግዚአብሔር ሞኝነት እንደሚልቅ ተረድቷልና፡፡ ሐዋ 17፥23፤ 1ቆሮ 1፥25:: ምንም ጥርጥር የለውም የአምላካችን ጥበብ ይልቃል ክብር ይግባው::
እግዚአብሔር በኃይሉም ይሁን በጥበቡ በራሱ ተወስኖ የሚኖር አምላክ አይደለም:: ኃይሉን በፍቅር አጋርቶናል:: ስለዚህ ነው “በሚወደን በእርሱ ከአሸናፊዎች እንበልጣለን” ፤ “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” ብለን የምናምነው::
እንግዲህ እግዚአብሔር ኃያልና የኃይላችንም ምንጭ ነው:: በመሆኑም መጽሐፍ እንደሚል የሚሳነው አንዳች ነገር የለም:: ሰው እንኳ በአቅሙ ብዙ ኃይለኛ መሣሪያዎችን ሠርቷል:: ይልቁንም የዘመናችን ትልቁ ሥጋት የሰው ልጅ አእምሮ ውጤት የሆነው ኒውክለር ነው:: በመሆኑም ኃይለኛ ሰው መሣሪያዎች መሥራት ከቻለ የሰውም ኃይል ታላቅ ነው:: ነገር ግን ሰው ምንም እንኳ ኃይል ጥበብና ብልሃት ያለው ፍጥረት ቢሆንም በሠራው ኃይለኛ መሣሪያ ይጠፋል:: ኃይለኛው እግዚአብሔር ግን ኃይለኞች የሆኑትን የሰው ልጆች የሠራ እርሱ ነው:: የሰው ኃይል በእርሱ ዘንድ የእሳት ትንታግ እንኳ አታክልም:: “ሰው በኃይሉ አይበረታምና ከእግዚአብሔር ጋር የሚጣሉ ይደቃሉ” ነው የተባለው:: የኃያላንን ቀስት ለመስበር ደካሞችን በኃይል ለማስታጠቅ የታመነ ነው:: እርሱ ሁሉን ይችላል:: ነገር ግን የማይችለው ደግሞ አለ:: ለመሆኑ እግዚአብሔር ምን የማይችለው ነገር አለ? ለባሕርዩ የማይስማማውን ነገር ሁሉ ሊያደርገው ወይም ሆኖ ሊገኝ አይችልም:: ይህም:
1. እግዚአብሔር ሊዋሽ አይችልም ቲቶ 1፥2
ውሸት የእውነት ተቃራኒ ነው:: ሐሰትና ውሸት ከአንድ ምንጭ የሚቀዱ ናቸው:: እነዚህ የእውነት ተቃራኒዎች ከዲያብሎስ የተገኙና ለደካማው የሰው ልጅ ፈተና ሆነው የሚኖሩ በመላዕክት ከተማ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገለጡ የኃጢአት ዓይነቶች ናቸው:: ሳጥናኤል የሰማያዊው ቤተመንግሥት አኃዜ መንጦላዕት ሆኖ እያገለገለ በነበረበት ወቅት ትዕቢት ከልቡ መነጨ:: በአንደበቱ ደግሞ ሐሰትን ወለደ:: ስለዚህም ነበር ጌታ በወንጌል “እርሱ /ዲያብሎስ/ ሐሰተኛ የሐሰትም አባት ነው” ያለው:: ዮሐ 8፥44 እውነትና የእውነት መገኛው እግዚአብሔር ሲሆን የተቃራኒው ደግሞ ዲያብሎስ መሆኑን ጌታ አስታውቆናል:: በመላዕክት ከተማ የዘራው ሐሰት ብዙ ደካማ መላዕክትን ሰብስቦለታል:: በኋላም በገነት ለአዳምና ለሔዋን ይህንኑ ሐሰት አቅርቦ የእግዚአብሔርን እውነት እንዲክዱ አምላክነትንም እንዲሹ አድርጓቸዋል:: ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ከእግዚአብሔር የተቀበለው ማንነት /ባሕርይ/ ስለተበከለበት ሐሰትን ተናጋሪ በመሆኑ ለዲያብሎስ የግብር ልጅ ሆኗል::
ነቢዩ ሙሴ እግዚአብሔር የማያደርገውን እንደማይናገር የማይፈጽመውን እንደማይጀምር ከገለጸ በኋላ ምንም ዓይነት አሉታዊ ነገር እንደሌለበትና እንደማይኖርበት ሲናገር “ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው አይደለም” ብሏል:: ዘኁ 23፥19:: ሙሴ እግዚአብሔርን መጀመሪያ ሐሰተኛ ከሆነው ከዲያብሎስ ጋራ ለምን አላነጻጸረውም? የእግዚአብሔር የመጨረሻው ፍጥረት ከሆነው ከሰው ጋራ ማነጻጸር ለምን አስፈለገው? ብሎ መጠየቅ ይቻላል:: መልሱም ምንም እንኳ ፈጠሪን ከፍጡር ጋር ማነጻጸር መልካም ባይሆንም፤ ሰው በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ ስለተፈጠረና የእግዚአብሔር የባሕርይ ተካፋይ ስለሆነ ከመላዕክት ይልቅ እግዚአብሔርን ከሰው ጋራ ማነጻጸር የተሻለ ስለሆነ ነው:: እግዚአብሔር በሰው ማንነት ራሱን ስለገለጸ ሰው ደግሞ በውስጡ ባለው በእግዚአብሔር ማንነት ከፍጥረት ከፍ ብሏል:: ሰው በተፈጥሮ ከመላዕክት ይበልጣል :: ሆኖም ሰው ከሥጋው ድካም የተነሣ እውነተኛውን ነገር ሐሰት የሚያለብስና የሚያጣምም ተቀያያሪ ማንነት ይታይበታል:: እግዚአብሔር ግን የማይለዋወጥና ቃሉ የታመነ ሥራውም እውነት ነው:: የእግዚአብሔር ምክር ለዘለዓለም ይኖራል:: የልቡም አሳብ ለልጅ ልጅ ነው እያለ ዳዊት የዘመረውን እናስተውለው፡፡ መዝ 32፥11:: በሌላ መልኩ መንፈስ ቅዱስ በመዝሙረኛው ዳዊት ሲናገር “በእውነቴ አልበድልም” ብሏል መዝ 88፥33:: እግዚአብሔር ለምንድን ነው መዋሸት ማይችለው? በመግቢያችን ላይ ለባሕርዩ ስለማይስማማ ነው ብለን ነበር:: በተጨማሪም እርሱ ከነገሮች ሁሉ በላይ ነው:: አሳቡ እንደ እኛ አሳብ አይደለም:: አኗኗሩም እንደ እኛ ከንቱነት ፈጽሞ የለበትም:: ሰው የሚዋሸው ሆን ብሎ ወይም ለነገሮች ማለፊያ ስለሚመስለው ነው:: እግዚአብሔር ግን አንድ ሁነት ከመታሰቡ በፊት ፍጻሜውን ደግሞም በሂደት ውስጥ የሚገጥመውን ውጣ ውረድና መፍትሔውን ሁሉ ያውቃል:: ታዲያ ስለምን ይዋሻል? እውነቱ ግልጽና ቃሉም ድርጊት ነው:: ስለዚህም ነው “ከቃሌ አንዲት ከምታልፍ ሰማይና ምድር ቢያልፍ ይቀላል ያለው:: ፍጥረት ሁሉ የቆመው በቃሉ ነውና:: ውድ ወገኔ እንግዲህ ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ግባና እግዚአብሔር ተናግሮ ያልተፈጸመ /ውሸት/ ሆኖ የቀረ ምን ነገር አለ? ምንም:: አንዳች ነገር የለም:: እርሱ ያለው ሁሉ ተፈጽሟል፤ እየተፈጸመ ነው፤ ይፈጸማል:: በመሆኑም እግዚአብሔር መዋሸት አይችልም::
2. እግዚአብሔር ራሱን ሊክድ አይችልም
ዓለማችን የብዙ ልዩነቶች ማኅደር ናት:: ቀለም፣ ጤና፣ ኑሮ፣ ትምህርት፣ ባሕል፣ አመለካከት፣ ማመን፣ መክዳት፣ ማፍቀር፣ መጥላት፣ መራብ፣ መጠማት፣ መወለድ፣ ማደግ፣ መኖር፣ መሞት እና የመሳሰሉት ልዩነቶች የተፈጥሮ ሂደት ውስጥ የምናገናኘቸው ማናችንም ብንሆንም የምናልፍባቸው ቀለበቶች ናቸው:: አዎንታዊ በሆነው አቅጣጫ ካየናቸው የዓለማችን ውበቶች ናቸው:: ማደግ ባይኖር ሕፃንነት የሚያሳሳ ልጅነትም የሚያጓጓ አይሆንም ነበር:: መሞት ባይኖር የመኖርን ጣዕምና ትርጉም ፍለጋ ማንም አይንቀሳቀስም ነበር:: ብቻ ውጤቱ መልካም ይሁን ክፉ ሁሉም የዓለም ውበቶች ለአስተዋይ ሰው ደግሞ ትምህርቶች ለመንፈሳውያን ደግሞ አምላካቸውን የሚያመሰግኑበት የምስጋና የጸሎት ምክንያቶች ናቸው::
በሌላ መልኩ ስንመለከታቸው ደግሞ እነዚህ ልዩነቶች የቀጣዩ ዓለም ወይም ዘመን ጥላዎች /ግልባጮች/ ናቸው:: ከቅዱሱ ውሃና መንፈስ ተወልዶ የእግዚአብሔር ልጅ የሆነና በክርስቶስ ሕያው ደም የታተመ አንድ አማኝ በዚህ ምድር መልክዓ ምድራዊ ክልል ተበጅቶለት የዚህ አገር ሰው የዚያ አገር ሰው እየተባለ ሲኖር ለዜግነቱ ማረጋገጫ የራሱ ፎቶ ያለበት ፓስፖርት ይዞ ሲንቀሳቀስ የሚረዳው አንድ እውነት አለ::
ይህም በዚህ አማኝ ላይ ያለው የአንድ ልጁ የኢየሱስ ክርስቶስ መልክ የዚህን ዓለም ድንበር መሻገሪያ እንደሚሆነውና ለዘላለም የሚኖርበት ሰማያዊ ሀገር እንዳዘጋጀለት፤ እዚህ ለጊዜው እንደሚኖር እዚያ ግን ለዘላለም እንደሚኖሩ ፣እዚህ የራሱ ወይም የሌሎች የገንዘብና የዕውቀት አቅም በቻለው መጠን በተሠራ ቤት እዚያ ግን በእግዚአብሔር ችሎታ በተሠራ ቤትና በተዘጋጀ ከተማ እንደሚኖር፤ እዚህ የተለያየ ፖለቲካዊ አመለካከት ባላቸው መሪዎች እየተመራ እዚያ ግን እረኛው አንድ መንጋውም አንድ ሆኖ በአንድ መንፈስና በአንድ ልብ እንደሚኖር ያውቃል:: ስለዚህ በዚህ ዓለም ያሉ ልዩነቶች የመጭው ዓለም ግልባጮች ናቸው::
እንግዲህ በዚያኛው ዓለም ፊት ለፊት የምናየውን እግዚአብሔር በዚህ ዓለም ብዙዎች በተለያየ የእምነት መጠን አምነውታል:: ብዙዎቹም በተለያየ የእውቀት መጠን አውቀውታል:: ብዙዎችም በተለያየ የሕይወት ልምምድ አብረውት ኖረዋል:: እንደ ጴጥሮስ እያመኑ እየካዱ፤ እንደ ቶማስ እየተጠራጠሩ እንደ ይሁዳ ከጌታ ይልቅ ገንዘብን እየወደዱ ግን አብረውት ኖረዋል:: በርግጥ አብሯቸው የመኖራቸው ምክንያት እነርሱ ለእርሱ ያላቸው ነገር አይደለም:: እርሱ ለእነርሱ ያለው ነገር ነው:: ስለሆነም እግዚአብሔር እንደ አማኞቹ ባሕርይ የሚሠራ አምላክ ሳይሆን እንደ ባሕርዩ የሚሠራ ነው:: በመሆኑም ሐዋርያው “ባናምነው እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል:: ራሱን ሊክድ አይችልምና” ይላል:: 2ጢሞ 2፥13:: እኛ በእምነት ብንዋልል፣ ብንዋዥቅ የእርሱን ማንነት ሊቀንስ ብናምነውም በእርሱ ማንነት ላይ ጥቂት ልንጨምር አንችልም:: እርሱ ታማኝ ነው፤ ጥንትም የነበረ፣ ዛሬም ያለ ወደ ፊትም የሚኖር ነው:: ራሱን ሊክድ አይችልም::
ስለሆነም ውድ ወገኔ ምንም እንኳ ያንተን በጎ ፈቃደኝነት የሚፈለግ ቢሆንም የመኖርህ ምስጢር አንተ ባለህበት ሁኔታ ውስጥ አምላክህ ካንተ ጋር ለመኖር ያለው ታማኝነት ነው:: አንዳንድ ጊዜ ራስህን መረዳት ተስኖህ ራስህን ስትኮንን ገጥሞህ ያውቃል? አንተነትህን መቀበል አቅቶህ ማንነትህን የረገምክበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? በራስህ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ባትችልም ሰው መሆንህን ለመካድ የጣርክባቸው ወቅቶች የሉም? በዚህ ሁሉ ጊዜ ውስጥ ግን ጌታህ አብሮህ ነበር:: እርሱ ላንተ ካንተ በላይ ታማኝ ነበርና:: ከዮሴፍ ጋር እስር ቤት የነበረው ጌታ ተጠራጣሪ ከነበረው ጴጥሮስ ጋር ባሕሩ ላይ ነበረ:: ዘፍ 39፥21፤ ማቴ 14፥34:: ዛሬም ደግሞ ያው ነው:: ቀኑ መሽቶ እስኪነጋ ዕድሜ ሊያሰጥህ የሚችል አንዳች ነገር ባይኖርህም በእርሱ ተደግፈህ ይነጋልሃል፤ ይመሽልሃልም:: መዝሙረኛው “በሰላም እተኛለሁ፤ አንቀላፋለሁ፣ አቤቱ አንተ ብቻህን በእምነት አሳድረኸኛልና” እያለ የሚዘምረውን አስተውለሃል? በእውነት በእምነት የተጠጋኸው ጌታ ራሱን ሊክድ አይችልም::መዝ 4፥8
3. እግዚአብሔር በክፉ ሊፈተን አይችልም
ፈተና የአንድን ሰው ወይም ነገር ብቃት ለማረጋገጥ የሚቀርብ ማጣሪያ ነው:: የሰውን ግንዛቤ አካላዊ ወይም ከጤና ጋር በተያያዘና ልምድን በተመለከተ ያለውን የደረጀ /የበሰለ/ ማንነት ለማወቅ የሚቀርብ ይሆናል:: ቁሳዊ ነገሮችን በተመለከተም ይዘቱን የአገልግሎት ዘመኑን የውስጥ /የውጭ/ ዕቃዎቹ በሙሉ ያላቸውን አቋም /ደህንነት/ ማጣሪያ ነው:: በሌላ አገላለጽ የሰውን ወይም የነገሮችን ደኅንነት ለመፈተሽ የሚቀርብ መመዘኛ ነው::
ሰው ሲፈተን ፈተናው የመጣው በዐይን ታይቶ ወይም በጆሮ ተሰምቶ ይሆናል:: ያየነው ወይም የሰማነው ነገር በውስጣችን ያለውን ደካማ ፍላጎታችንን ይቀሰቅስና ፈተና ውስጥ እንገባለን:: ቅዱስ ያዕቆብ “እያንዳንዱ በራሱ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ይፈተናል” ያለው ለዚህ ነው:: ያዕ 1፥14:: በሥጋዊውም ይሁን በመንፈሣዊ ሕይወት ውስጥ ያሉ ፈተናዎች ዓለም ዓቀፋዊ ናቸው:: ክርስቲያን ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም በመኖሩ ማንኛውም ሰው በኑሮ ውስጥ ሊገጥመው የሚችለውን ፈተና ይፈተናል:: በጤና፣ በሥራ፣ በቤተሰብ፣ በማኅበራዊ ሕይወት፣ በሀገር አስተዳደር አለመረጋጋት ውስጥ የሚፈጠሩ ፈተናዎች ሁሉ ለማንኛውም ሰው የጋራ ፈተናዎች ናቸው:: በሌላ መልኩ ደግሞ መንፈሳዊ ሰው ስለሆነ የሚገጥሙት ፈተናዎች ይኖራሉ:: እርሱ መንፈሳዊ ሰው ስለሆነ “እንደ እግዚአብሔር ቃል ለመኖር በሚያደርገው ጉዞ ውስጥ ሰይጣን፣ ዓለምና የራሱ ድካም መሰናክል ሊሆኑበት ይችላሉ:: በዚህ ይፈተናል::
እንዲሁም የእግዚአብሔርን ቃል ለራሱ በሚመቸው መንገድ ከራሱ ሐሳብ ጋር ለማስማማት ሲጥር ወይም እርሱ ወደ እግዚአብሔር ቃል ከመሄድ ይልቅ የእግዚአብሔርን ቃል ወደ እርሱ ማምጣት ሲፈልግ ይፈተናል:: መንፈሳዊ ሰው መኖር ያለበት ግን እንደ እግዚአብሔር ቃል ነው:: “ለክርስቶስ ወንጌል እንደሚገባ ኑሩ” ነው የተባለው እንጂ ወንጌሉ ለእናንተ እንደሚገባ ይኑር” አይደለም የተባለው:: ወንጌል የእኛ ሕይወት የሚለካበት፣ የሚመዘንበት ነው:: ተመዛኞቹ እኛ ነን እንጂ ወንጌሉ አይደለም:: ስለዚህ በዚህ መልኩ ፈተና ሊመጣብን ይችላል::
ነገር ግን ፈተና ዓለም ዓቀፋዊ ቢሆንም እግዚአብሔር በክፉ ሊፈተን አይችልም:: ንጹሕና ቅዱስ የሆነው አምላክ በባሕርዩ ክፉ መሻት ደካማ ማንነት ስለሌለበት ከውጭ በሚመጣ ፈተና ተጽዕኖ ውስጥ ሊወድቅ አይችልም:: አስቀድሞ ከካደው ከሳጥናኤል ጊዜ ጀምሮ አዳም እስከ ካደበት ብሎም እስከ ዓለም ፍጻሜ እግዚአብሔር በፈጠረው ፍጥረት ያልተፈተነበትና የማይፈተንበት ዘመን የለም:: የሚቀርቡለት ፈተናዎቹ የሚያስጸጽቱት፣ የሚያስቆጡትና የሚያሳፍሩት ሊሆኑ ይችላሉ:: ይልቁንም ጌታ ኢየሱስ የተቀበላቸውን ፈተናዎች በሰብኳቸው ጊዜ ሕሊናዬ ይናውዛል፡፡ትንሣኤውንና ዕርገቱን ሳስብ ደግሞ አንደበቴ በእልልታ ይመላል፡፡ይሁን እንጂ ለሚፈተኑ አማኞች ከፈተና የመውጫውን መፍትሔ የሚሰጥ እርሱ ከራሱ በሚነሳ ድክመት ሊፈተን አይችልም::
ጸጋ ይብዛላችሁ !!! እንደ ቃሉ እንኑር !
No comments:
Post a Comment