ክፍል አራት
በጸጋ መጠራት 1፥6
“በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ . . .”
ጸጋ “ካሪዝ” ከሚለው የግሪክ ቃል ትርጉም የሚገኝ ሲሆን በእብራይስጡ ደግሞ “ሞገስ” “ፍቅር” “ምሕረት” “ቸርነት” የሚሉትን ቃላት አሳብ የሚይዝ ነው:: ጸጋ እግዚአብሔር በደለኛ ለሆነው ለሰው ልጅ የሰጠው ነጻ ስጦታ ነው:: ሕግ ደግሞ የሰው ኃጥአተኝነትንና ተላላፊነትን የሚያሳይ ነው፡፡ የሰው ተግባር መለኪያ ነው፡፡ በራሱ አያድንም፡፡ ማዳን ወደሚችለው ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ነው፡፡
ወንጌላዊው ዮሐንስ “ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነ” ይላል ዮሐ 1፥17:: ዮሐንስ በዚህ ሐረግ ውስጥ በሁለቱ ኪዳናት (በብሉይ እና አዲስ ኪዳን) ውስጥ የሚገኙ ሁለት ታላላቅ መሠረቶችን ይገልጻል:: እነዚህም ሕግና ጸጋ ናቸው:: ሁለቱም ሙሴ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ይታወቁባቸዋል::
ሕግ የመጣው በሙሴ ጸጋ የመጣው ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው :: ሁለቱም የሚፈልጉት ነገር ይለያያል:: ሕግ ሥራን ሲፈልግ ጸጋ ደግሞ እምነትን ብቻ ይፈልጋል:: ሕግ የሚያስገኘውን ሽልማት ሕጉን በመፈጸም መቀበል ሲቻል ጸጋ የሚያስገኘውን ሽልማት ደግሞ በማመን ብቻ መቀበል ይቻላል:: ይህም በሕግ ውስጥ ጸጋ /እንዲሁ የሚሰጥ/ አለመኖሩን እና በጸጋ ውስጥ ደግሞ ሕግ /በተግባር የሚገኝ/ አለመኖሩን ያስረዳል፡፡ ከሕጉ ውስጥ በአንዱ የተሰናከለ የሌሎቹንም ዋጋ በዚያው ያጣል:: “ሕግን ሁሉን የሚጠብቅ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል” ይላልና:: ያዕ 2፥10::
ሕግ የእግዚአብሔርን ንጹሕ ባሕርይ ያሳያል:: ከልካይ ሕግ ሳይኖርበት ያለ ኃጢአት የሚኖር እርሱ ብቻ ነውና:: እንዲሁም በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ የሚኖርም ኃጢአት ለማይስማማው ለእግዚአብሔር ፈቃድ በሚገባ መጠን በንጽሕና መኖር እንደሚያስፈልግ ያስታውቃል:: ሆኖም ይህ ለሰው አልተቻለም:: ጸጋ አስፈላጊ የሆነው ሕግ የሰውን ጥንካሬና የማይለወጥ የንጽሕና /የቅድስና/ አቋም ሲፈልግ ሰው ግን ደካማ ሆኖ በመገኘቱ ነው:: ስለዚህ ሰው እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ሆኖ እንዲገኝ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ዘንድ በሚታወቅበት ማንነት መጠራት ነበረበት:: ይህም ማንነት “ልጅነት” ነው:: ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው:: ሰውም የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት ሲያምን በእምነቱ በኩል የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል:: ሕግ ለባርነት ይጠራል:: ጸጋ ደግሞ ለልጅነት ይጠራል:: ሐዋርያው በዚሁ መልዕክት ላይ “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ” ብሏል:: ገላ 3፥6::
ሐዋርያው “በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ” በማለት “ከእርሱ” የሚለውን ሦስተኛ መደብ ተውላጠ ስም የተጠቀመው “እግዚአብሔርን” ለመጥቀስ ነው:: እግዚአብሔር እኛን የጠራን በክርስቶስ ጸጋ ነው:: ይህ በቀደመው ዘመን ከእግዚአብሔር ወደ ሰው ከተላለፉት ጥሪዎች ሁሉ የሚለይ ጥሪ ነው:: በመጀመሪያ የእግዚአብሔር የፍለጋ ድምጽ ወደ ሰው ልጅ የመጣው በገነት ነበር:: በኋላም የሰው ልጅ በበደልና በኃጢአት ተወርሶ ጥፋትና ርኩሰት በሞላት ክፉ በሆነው በዲያብሎስ በተያዘች ዓለም ውስጥ ሲኖር የእግዚአብሔር የጥሪ ድምጽ አልተቋረጠም:: እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቷል፤ ሙሴን ለመሪነት ጠርቷል፤ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ለአምልኮ ነጻነት ጠርቷል:: ሆኖም ግን ይህ ጥሪ ሁሉንም በክርስቶስ ለሚደረገው የጸጋ ጥሪ የሚያዘጋጅ ነበር:: በሌላ አገላለጽ አብርሃምም ቢጠራ ከዑር (ካራን) ወጥቶ ርስት ተደርጋ የተሰጠችው ከነዓን ናት:: ሙሴም ቢጠራ ከፈርዖን ቤት ወጥቶ /በግብፅ ሕዝብ ላይ መስፍን እንዳይሆን/ በእግዚአብሔር ቤት እንዲኖርና በሕዝቡ ላይ ሊሾም ነው:: ስለዚህ የቀደሙት ጥሪዎች በምድራዊ ነገር ላይ የተመሠረቱ ነበሩ::
በጸጋ መጠራት ግን ልዩ ነው:: ጠሪው ራሱ የእግዚአብሔር ልጅ በተጠሪዎቹ መካከል በአካል ተገኝቷል:: እርሱ በምድር ከምድራዊያን ሰዎች ጋር ሳለ በሰማይም እስከነ ሙሉ ክብሩ አለ:: ጥሪው በሰማያዊና መንፈሳዊ ነገር ላይ የተመሠረተ ነው:: ስለዚህም ነው የዕብራውያን ጸሐፊ “ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ወንድሞች ሆይ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ” እያለ የጠሪውንና የጥሪውን እንዲሁም ጥሪውን የተቀበልነው እኛ የምናገኘውን መንፈሳዊ ነገር የሚያመለክተው፡፡ ጥሪውን የተቀበልን ሁሉ የምናገኘው ነገር ደግሞ “የክርስቶስን ክብር” ነው:: ይህም ክብር ሕያው ከሆነውና ከማይጠፋው ዘላለማዊ ዘር በመወለድ የሚገኝ ልጅነት ነው:: “ስለዚህም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር ለማግኘት በወንጌላችን ጠራችሁ” ተብለናል:: 2ተሰ 2፥14::
እግዚአብሔር በክርስቶስ ጸጋ ባስተላለፈው ጥሪ ቃሉን የሚፈጽሙ ብርቱዎችና ኃያላን የተባሉት ቅዱሳን መላዕክት አልተጠሩም:: እኛ በጸጋ በተቀበልነው ልጅነት ዓይነት የእግዚአብሔር ልጆች አልሆኑም:: እኛ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን የልጅነት ኅብረት መላዕክት አላገኙትም:: አብ ወልድን ይወዳል:: እንዲሁም ወልድን (ኢየሱስን) በወደደበት የፍቅር መጠን ልጁን ያመነውን እኛን ወዷል:: ጌታችን ኢየሱስም በታላቁ ጸሎቱ “አባት ሆይ ዓለም አላወቀህም እኔ ግን አወቅሁህ እነዚህም አንተ እንደ ላክኸኝ አወቁ፤ እኔንም የወደድህባት ፍቅር በእነርሱ እንድትሆን” ብሏል:: ዮሐ 17፥26::
እግዚአብሔር ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን አንድያ ልጁን በወደደበት ፍቅር ወዶናል:: ይህም በጸጋ በመጠራታችን ያገኘነው ነው:: ቅዱስ ዮሐንስ በመልዕክቱ “ፍቅርም እንደዚህ ነው እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተሰሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደላከ እንጂ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም” ብሏል:: 1ዮሐ 4፥10:: እንዲሁም በእግዚአብሔር መወደዳችን ያስገኘልንን ኅብረት ሲገልጽ “ኅብረታችን ከአባት ጋር ከልጁም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ነው” ይላል 1ዮሐ 1፥3:: ኅብረት ሲል የወይን ግንድ ከቅርንጫፎቹ ጋር ወይም በራስና በተቀረው አካል መካከል እንዳለው ግንኙነት እኛም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን መንፈሳዊ ግንኙነት /ኅብረት/ ይገልጻል:: ኅብረቱ የተገኘው በክርስቶስ ሥራ ነው:: “በእርሱ ሥራ ሁላችን በአንድ መንፈስ ወደ አብ መግባት አለን” ተብሏል:: ኤፌ 2፥18:: ወደ አብ መግባት ማለት አባት ለልጁ ለኢየሱስ ክርስቶስ ባለው ቅርበትና አንድነት ከእኛም ጋር መሆኑን መግለጽ ነው:: ይህ ደግሞ ሕያው ግንኙነት ይባላል::
በክርስቶስ ጸጋ የተጠራን ስለሆንን የሚያስፈልገንም ይሁን የምንፈልገውን ያገኘነውና የምናገኘው እንዲሁ በጸጋ ነው:: ጽድቅ፣ ቅድስና፣ ሕይወት፣ ቤዛነትና የመሳሰሉትን ሁሉ ያገኘነው በጸጋ ነው:: የምንከፍለው ወይም የከፈልነው አንዳች ዋጋ የለም:: ዮሐንስም በወንጌሉ “ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ ሆነ” ብሏል:: ዮሐ 1፥16::
እንግዲህ ከደረሰን ሰማያዊ ጥሪ ጋር ራሳችንን ስናነጻጽር የተደረገልን ነገር ሁሉ ከጸጋው የተነሣና የጸጋው ክብር እንዲመሰገን ነው:: እግዚአብሔር በክርስቶስ ጸጋ እኛን በመጥራቱ :-
· የምሕረቱ ብልጽግና ተገልጿል ኤፌ 2፥4-5
· የፍቅሩ ታላቅነት ታውቋል
· ሕግ የትም እንደማያደርስ ታይቷል
· ድኅነት በእምነት ሆኗል
· እግዚአብሔርን አባት ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብለናል
· የልጅነት ሥልጣን አግኝተናል፤ የእግዚአብሔር ከሆነው ነገር ሁሉ ተጠቃሚ ነን::
ጸጋ ይብዛላችሁ !!!
ለአዲሱ ፍጥረት/ለቤተክርስቲያን ህግ መሰበክ አለበት ወይስ ፀጋ ብቻ?
ReplyDelete