ክፍል አራት
በጸጋ መጠራት 1፥6
“በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ . . .”
ጸጋ “ካሪዝ” ከሚለው የግሪክ ቃል ትርጉም የሚገኝ ሲሆን በእብራይስጡ ደግሞ “ሞገስ” “ፍቅር” “ምሕረት” “ቸርነት” የሚሉትን ቃላት አሳብ የሚይዝ ነው:: ጸጋ እግዚአብሔር በደለኛ ለሆነው ለሰው ልጅ የሰጠው ነጻ ስጦታ ነው:: ሕግ ደግሞ የሰው ኃጥአተኝነትንና ተላላፊነትን የሚያሳይ ነው፡፡ የሰው ተግባር መለኪያ ነው፡፡ በራሱ አያድንም፡፡ ማዳን ወደሚችለው ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ነው፡፡
ወንጌላዊው ዮሐንስ “ሕግ በሙሴ ተሰጥቶ ነበርና ጸጋና እውነት ግን በኢየሱስ ክርስቶስ የሆነ” ይላል ዮሐ 1፥17:: ዮሐንስ በዚህ ሐረግ ውስጥ በሁለቱ ኪዳናት (በብሉይ እና አዲስ ኪዳን) ውስጥ የሚገኙ ሁለት ታላላቅ መሠረቶችን ይገልጻል:: እነዚህም ሕግና ጸጋ ናቸው:: ሁለቱም ሙሴ እና ኢየሱስ ክርስቶስ ይታወቁባቸዋል::
ሕግ የመጣው በሙሴ ጸጋ የመጣው ደግሞ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው :: ሁለቱም የሚፈልጉት ነገር ይለያያል:: ሕግ ሥራን ሲፈልግ ጸጋ ደግሞ እምነትን ብቻ ይፈልጋል:: ሕግ የሚያስገኘውን ሽልማት ሕጉን በመፈጸም መቀበል ሲቻል ጸጋ የሚያስገኘውን ሽልማት ደግሞ በማመን ብቻ መቀበል ይቻላል:: ይህም በሕግ ውስጥ ጸጋ /እንዲሁ የሚሰጥ/ አለመኖሩን እና በጸጋ ውስጥ ደግሞ ሕግ /በተግባር የሚገኝ/ አለመኖሩን ያስረዳል፡፡ ከሕጉ ውስጥ በአንዱ የተሰናከለ የሌሎቹንም ዋጋ በዚያው ያጣል:: “ሕግን ሁሉን የሚጠብቅ ነገር ግን በአንዱ የሚሰናከል ማንም ቢኖር በሁሉ በደለኛ ይሆናል” ይላልና:: ያዕ 2፥10::
ሕግ የእግዚአብሔርን ንጹሕ ባሕርይ ያሳያል:: ከልካይ ሕግ ሳይኖርበት ያለ ኃጢአት የሚኖር እርሱ ብቻ ነውና:: እንዲሁም በእግዚአብሔር ፈቃድ ውስጥ የሚኖርም ኃጢአት ለማይስማማው ለእግዚአብሔር ፈቃድ በሚገባ መጠን በንጽሕና መኖር እንደሚያስፈልግ ያስታውቃል:: ሆኖም ይህ ለሰው አልተቻለም:: ጸጋ አስፈላጊ የሆነው ሕግ የሰውን ጥንካሬና የማይለወጥ የንጽሕና /የቅድስና/ አቋም ሲፈልግ ሰው ግን ደካማ ሆኖ በመገኘቱ ነው:: ስለዚህ ሰው እግዚአብሔር እንደሚፈልገው ሆኖ እንዲገኝ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ዘንድ በሚታወቅበት ማንነት መጠራት ነበረበት:: ይህም ማንነት “ልጅነት” ነው:: ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ ነው:: ሰውም የኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝነት ሲያምን በእምነቱ በኩል የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል:: ሕግ ለባርነት ይጠራል:: ጸጋ ደግሞ ለልጅነት ይጠራል:: ሐዋርያው በዚሁ መልዕክት ላይ “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁ” ብሏል:: ገላ 3፥6::
ሐዋርያው “በክርስቶስ ጸጋ እናንተን ከጠራችሁ ከእርሱ” በማለት “ከእርሱ” የሚለውን ሦስተኛ መደብ ተውላጠ ስም የተጠቀመው “እግዚአብሔርን” ለመጥቀስ ነው:: እግዚአብሔር እኛን የጠራን በክርስቶስ ጸጋ ነው:: ይህ በቀደመው ዘመን ከእግዚአብሔር ወደ ሰው ከተላለፉት ጥሪዎች ሁሉ የሚለይ ጥሪ ነው:: በመጀመሪያ የእግዚአብሔር የፍለጋ ድምጽ ወደ ሰው ልጅ የመጣው በገነት ነበር:: በኋላም የሰው ልጅ በበደልና በኃጢአት ተወርሶ ጥፋትና ርኩሰት በሞላት ክፉ በሆነው በዲያብሎስ በተያዘች ዓለም ውስጥ ሲኖር የእግዚአብሔር የጥሪ ድምጽ አልተቋረጠም:: እግዚአብሔር አብርሃምን ጠርቷል፤ ሙሴን ለመሪነት ጠርቷል፤ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ለአምልኮ ነጻነት ጠርቷል:: ሆኖም ግን ይህ ጥሪ ሁሉንም በክርስቶስ ለሚደረገው የጸጋ ጥሪ የሚያዘጋጅ ነበር:: በሌላ አገላለጽ አብርሃምም ቢጠራ ከዑር (ካራን) ወጥቶ ርስት ተደርጋ የተሰጠችው ከነዓን ናት:: ሙሴም ቢጠራ ከፈርዖን ቤት ወጥቶ /በግብፅ ሕዝብ ላይ መስፍን እንዳይሆን/ በእግዚአብሔር ቤት እንዲኖርና በሕዝቡ ላይ ሊሾም ነው:: ስለዚህ የቀደሙት ጥሪዎች በምድራዊ ነገር ላይ የተመሠረቱ ነበሩ::