ጸሎት
የማትመረመር ሁሉን የምትመረምር፤ የማትታይ ሁሉ በፊትህ የተገለጠና የተራቆተ፤ ሐሳባችንን የምታነብ በልባችን የሚመላለሰውን ምኞት የምትሰማ እግዚአብሔር ሆይ አባታችን ነህና ተመስገን:: ጌታችን ሆነህ የመገዛት ጸጋን ሰጥተኸናልና ተመስገን:: አምላካችን ሆነህ የአምልኮ መንፈስን ሰጥተኸናልና ተመስገን:: የጠፋውን ፈልገህ የምታመጣ ከበረትህም የምታስገባ የወደቀውን የምታነሣ የደከመውን በቃልህ ጉልበት የምታበረታና ለክብርህም የምታቆም አንተ ነህና ተመስገን::
የምንታመንለትን እውነት የምንጓዝበትን መንገድ የምንኖርበትን ሕይወት አንድ ልጅህን ጌታ ኢየሱስን ስለሰጠኸን ደግሞም አንተንና እርሱን በንጹሕ ዕምነት ማወቅንም የዘላለም ሕይወት ስላደረግህልን ተመስገን:: አንተን በማመን እንድንጸና በቃልህ በኩል መጽናናት እንዲሆንልን የፍቅርህ መልዕክት የሆነውን ቅዱስ መጽሐፍ ስለሰጠኸን ተመስገን::
ጌታ ሆይ በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ያለውን እውነት በማስተዋል እንድንረዳ ዐይነ ልቡናችንን ታበራ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን:: አሜን!!
መቅድመ ነገር
መጽሐፍ ቅዱስ ለምን ይጠናል?
የሰው ልጅ ባለአእምሮ ፍጥረት ነው:: ገና ጠባብና ምቹ ከሆነው ከእናቱ ማኅጸን ሰፊና አስቸጋሪ ወደሆነው ወደ ገሃዱ ዓለም ሲመጣ ማየት የሚችል ዐይን መስማት የሚችል ጆሮ መዳሰስ የሚችል እጅ እንዲሁም አጠቃላይ ሰውነት መቅመስና ጣዕምን መለየት የሚችልበት ምላስ ማሽተትና መዓዛን መለየት የሚችልበት አፍንጫ ይዞ ነው የሚወለደው::
ይሁን እንጂ ከዚህ በላይ ለጠቀስኳቸውና በቁጥር ለመወሰን አስቸጋሪ ለሆኑት ስሜቶቹ ሁሉ ዋናውንና አስፈላጊውን እገዛ የሚሰጠው የሰውነቱ /የብልቶቹ ሁሉ/ ዋናው መሥሪያ ቤት (አዛዥ ባለስልጣን) አእምሮው ነው:: እንዲያውም በሰው ልጅ የአወላለድ ሂደት በመጀመሪያ የገሃዱን ዓለም የሚቀላቀለው ጭንቅላቱ /ራሱ/ ነው:: ጠንካራ በሆነውና ከአጥንት በተገነባው ደግሞ የአጥንቱ ስፌት በሚያምረው የራስ ቅል ውስጥ ያለውን የሰው ልጅ ሁሉን ነገር የሚያውቅበትን የሚረዳበትን የሚገነዘብበትን ዋናውን የሰውነቱን ክፍል ይዞ ይወለዳል:: ዐይን፣ ጆሮና ሌሎችም የስሜት ሕዋሳት አጠቃላይ መረጃን በመሰብሰብ ለአእምሮ ያቀብላሉ:: አእምሮ ደግሞ የተቀበለውን መረጃ በየዐይነቱ በመለየት ያደራጃል፤ ያገናዝባል፤ ያብሰለስላል፤ ያንሰላስላል። በመቀጠልም አስፈላጊ የሆነውን ትርጉም በመስጠት ዕውቀት ያደርገዋል።
እንግዲህ ቁሳዊ በሆነው በዚህ ዓለም የሚኖረው የሰው ልጅ ሥጋዊ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ የሆኑትን እንዲሁም ተፈጥሮአዊ ጉዳዮችን ሁሉ ማጥናቱ የተለመደ ነው። ምክንያቱም ለማወቅ መፈለግና ማወቅ ተፈጥሮአዊ ስጦታው ነውና። ስለሆነም ሰው ይልቁንም ክርስቲያን ሊያጠናቸው ከሚገቡት ነገሮች ውስጥ ቅድሚያ መስጠት ያለበት ለመጽሐፍ ቅዱስ ነው። ጥናት ከሚጠናው ነገር ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ግንኙነት ያላቸውን መረጃዎች በማሰባሰብና በማመሳከር ስለሚጠናው ነገር ጥልቅ ጭብጥ ወይም ጥቅል እውነት ላይ መድረስ ነው። ስለሆነም መጽሐፍ ቅዱስ ከሚጠናበት ምክንያቶች ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው።
1. እምነትን ለማጠንከር
እምነት የማናየውንና ተስፋ የምናደርገውን ነገር የሚያረጋግጥ ከሰው ልጅ የአማኝነት ተፈጥሮአዊ ዝንባሌ ውስጥ የሚፈልቅና የሚያድግ መንፈሳዊ ኃይል ነው። የሚያድግ ብቻም ሳይሆን የሚያሳድግም ነው፡፡“እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደተቀበላችሁት (እንዳመናችሁት)በእርሱ ተመላለሱ ሥር ሰዳችሁም በእርሱ ታነጹ” በተባለውም መሠረት ክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ ስለኃጢአታችንም ተላልፎ የተሰጠ ቤዛችን መሆኑን በማመን መንፈሳዊ ቤት ለመሆን የምንታነጽበት ነው። ቈላ 2፥6። እንዲሁም በዚህ በዘመን መጨረሻ ላይ የምንገኝ ክርስቲያኖች የእምነታችንን ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን የምናይበት (የምንመለከትበት)ዐይናችንም ነው። ዕብ 12፥2። ደግሞም ድኅነትን ያገኘንበትን ጸጋ የተቀበልንበት ነው። ኤፌ 2፥8። ቅዱስ ዮሐንስም በወንጌሉ የእረኛችንን ድምጽ ከጠላት ድምጽ ለይተን የምናውቅበት መሆኑን “በጎቹ ድምጹን ያውቃሉና ይከተሉታል” በማለት ይገልጻል። ድምጹን ማወቅ መስቀላችንን ተሸክመን እንድንከተለው ያስችለናል። ዮሐ 10፥4። የእረኛችን ድምጽ በቅዱሳን ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ተጽፎ የተቀመጠልን መጽሐፍ ቅዱስ ስለሆነ ቃሉን ማወቅ እምነትን ማሳደግና እንዲያብብ ማድረግ ከዚያም የመንፈስ ፍሬ እንዲያፈራ ያስችላል፡፡
እንደየአማኙ ሁኔታ ታናሽ፣ ጎዶሎ፣ የሚያድግ፣ ታላቅ እምነት ሊኖረን ይችላል። ታናሹም ወደ ታላቅነት፤ ጎዶሎውም በክርስቶስ ወደሚገኝ ሙላት ፤ የሚያድገውም የወይን ግንድ በሆነው በክርስቶስ ሆኖ ፍሬ ማፍራት ታላቁም ከነውርና ከነቀፋ ርቆ ንጽሕናን ጠብቆ በቅድስና እየተመላለሰ እግዚአብሔርን በመምሰል መኖር የሚችለው ቃሉን በእምነት ሆኖ በማጥናት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ቃል በሙላት ይኑርባችሁ” ያለው እምነታችን በእውነትና በመንፈስ ከእግዚአብሔር ጋር የሚያቆመን እንዲሆን በቃሉ መጠንከር ስላለበት ነው፡፡ እንዲህ ከሆነ ደግሞ በውስጣችን ካለው ከእግዚአብሔር ቃል የተነሳ ፈቃዳችን ሁሉ ለእርሱ የተሰጠ ይሆናል፡፡ ቈላ 3፥16። “ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ” ተብሎ የተነገረላቸው የቤርያ ሰዎች የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት ሰምተው ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር ለማመሳከር ወደ ምርምር የገቡት መጻሕፍትን ማጥናት በእምነታቸው ላይ የሚጨምረውን ጥንካሬና ዕድገት በማስተዋል ነው። ሐዋ 17፥11። በእግዚአብሔር ቃል እምነቱ የጠነከረለት አማኝ ደግሞ
· ያመነውን ያውቃል 2ጢሞ 1፥12
· በወንጌል አያፍርም ሮሜ 1፥16
· እግዚአብሔርን ብቻ ይሰማል ሐዋ 4፥19
· ወደ ግራም ወደ ቀኝም አይልም ኢያ 1፥7
· ስለ ኃጢአቱ ያለቅሳል ማቴ 26፥75 እነዚህና የመሳሰሉት ጥቅሞች ስለሚኖሩት መጻሕፍትን በማጥናት እምነትን ማጠንከር አግባብ ነው።
2. ለመታዘዝ
መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና ለቃሉ በመታዘዝና ባለመታዘዝ የሚኖረውን የአቋምና የሕይወት ልዩነት እንረዳለን። ለቃሉ መታዘዝ የጽድቅ ባርያ /አገልጋይ/ ሲያደርግ አለመታዘዝ ደግሞ የኃጢአት ባርያ ያደርጋል። ስለዚህ ቃሉን ማጥናት ለተረዱት እውነት ለመታዘዝ መሆን አለበት። ይህን መድረሻ ግቡ አድርጎ የሚያጠና ሰው የጥናቱ መሠረት እምነት ስለሚሆን ላወቀው እውነት መታዘዝ አይከብደውም። የእግዚአብሔር ቃል ባጠናነው ቁጥር እምነታችንን እንደሚያጠናክር ሁሉ አመለካከታችንን ያስተካክላል፤ ግንዛቤያችንን ያሰፋል፤ ጠንካራውንም ልባችንን ይሰብራል። እንድንኖረውም ያስችለናል። መታዘዝ በተረዱት እውነት መኖር ማለት ነውና። በጌታ ዘመንም ይሁን በሐዋርያት ዘመን ለወንጌሉ አገልግሎት እንቅፋት ሆነው የነበሩት የአይሁድ ካህናት የእግዚአብሔር ቃል እየሰፋ ሲሄድ እነርሱም እውነቱን ሲረዱ ብዙዎቹ ለእግዚአብሔር ቃል ታዝዘዋል። ሐዋ 6፥7። ጌታም በወንጌሉ ምሳሌ መስሎ ሲያስተምር ለቃሉ የሚታዘዘውን ልባም ሰው ሲለው ለቃሉ የማይታዘዘውን ደግሞ ሰነፍ ሰው በማለት ገልጾታል። ማቴ 7፥24። ቅዱስ ያዕቆብም ለተበተኑት ክርስቲያኖች በጻፈው መልዕክቱ ”ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ“ ብሏል ያዕ 1፥22።
መታዘዝ በሥጋዊም ሕይወት ይሁን በመንፈሳዊ ሕይወት ውስጥ ያለው ጠቀሜታ በቃል ተዘርዝሮ በጽሑፍ ተተንትኖ የሚያልቅ አይደለም። አንድ የሥነ ሕንጻ ባለሙያ ለተማረውና ላጠናው ትምህርት ታዛዥ ሲሆን እጅግ በጣም ጥሩ ሙያተኛ ይሆናል። በጊዜ ሂደትም ትምህርቱን በተግባር ሲያዳብረው ደግሞ በጣም ተፈላጊና በሥራው ስኬታማ ይሆናል። አንድ መጽሐፍ ቅዱስ አጥኚ የሚያጠናው ለተረዳው እውነት ለመታዘዝ ከሆነም በቃሉ አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረው ኅብረት እየጠነከረ ዘወትር የእግዚአብሔር ፈቃድና እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር በመሥራት ይተጋል። መታዘዝ በድርጊት ይገለጣልና።